ሱዳን፡ ጄነራል አል ቡርሐን በቀጣዩ የሱዳን መንግሥት ውስጥ አልሳተፍም አሉ

ጄነራል አል ቡርሐን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የሱዳን ጦር ኃይል አዛዥ ጄነራል አብዱልፋታህ አል ቡርሐን ከሽግግሩ መንግሥት በኋላ የሚመሰረተው መንግሥት አካል እንደማይሆኑ ከአልጀዚራ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናገሩ።

በተጨማሪም ጄነራሉ ሠራዊታቸው ባለፈው ወር የተካሄደውን መፈንቅለ መንግሥት የተቃመሙ ዜጎችን ገድሏል መባሉን አስተባብለዋል።

"ብቃት ላለው የሲቪል መንግሥት ሥልጣን ለማስረከብ ቁርጠኞች ነን። ሽግግሩን ሊያደናቅፍ የሚችል ማንኛውንም ጣልቃ ገብነት ለመከላከል ቃል እንገባለን" ብለዋል።

የሱዳን ሐኪሞች ኮሚቴ መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም በተከናወኑ ሰልፎች ላይ ቢያንስ 14 ተሳታፊዎች መገደላቸውን እና ወደ 300 የሚጠጉ መቁሰላቸውን ገልጿል።

ሆኖም ጄነራል አል ቡርሐን ሠራዊቱ ሰዎችን አለመግደሉን እና ለሞቾቹ ኃላፊነት እንደማይወስድ ገልጸዋል።

"የሱዳን ጦር ዜጎችን አይገድልም። ምን እንደተፈጠረ የሚያሳውቁ የምርመራ ኮሚቴዎች አሉ" ብለዋል።

እንደ አልጀዚራ ዘገባ፤ "የሱዳን ፖለቲካዊ ጉዳዮች በርካታ መሰናክሎች ቢኖሩበትም በሚቀጥሉት 24 ሰዓታት ውስጥ በሽግግር መንግሥቱ የሥልጣን መጋራትን በተመለከተ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ ተስፋ አደርጋለሁ" ሲሉ ጄነራሉ ተናግረዋል።

በሱዳን ላለው ፖለቲካዊ ቀውስ መፍትሔ ለማበጀት የአረብ ሊግ የልዑካን ቡድን ወደ ካርቱም አቅንቶ እንደነበርም ተዘግቧል።