የሞዴሏን ፀጉር ያለ ፍቃዷ የቆረጠው የውበት ሳሎን 271 ሺህ ዶላር ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከዓመታት በፊት የአንዲት ሞዴልን ፀጉር ያለ ፍቃዷ አሳጥሮ ቆርጧል የተባለ የውበት ሳሎን 271 ሺህ ዶላር እንዲቀጣ የሕንድ ፍርድ ቤት ወሰነ።
ሞዴሏ ረዥም ፀጉር ስላላት የፀጉር ቅባት አምራቾች ለማስታወቂያ ይቀጥሯት ነበር። ሆኖም ግን ፀጉር ቤቱ ያለ ሞዴሏ ፍቃድ ፀጉሯን በመቁረጡ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባት በፍርድ ቤቱ ተነግሯል።
ዴልሂ የሚገኝ ታዋቂ ሆቴል ውስጥ ያለው ፀጉር ቤቱ የፍድር ቤቱ ውሳኔ ላይ ይግባኝ ማለት ይችላል ተብሏል።
በድርጅቶችና አገልግሎት በሚሰጧቸው ዜጎች መካከል የሚፈጠር አለመግባባትን የሚዳኘው ኮሚሽን እንዳለው፤ ሞዴሏ ፀጉሯ በመቆረጡ ምክንያት ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ ደርሶባታል። ስመ ጥር ሞዴል የመሆን ህልሟም እንቅፋት ገጥሟታል።
ፍርድ ቤቱ "በፀጉር ቤቱ ችላ ባይነት የተነሳ ከፍተኛ የአእምሮ መረበሽ ውስጥ ገብታለች። ፀጉሯ በመቆረጡ የተነሳ ሥራዋን አጥታለች" ተብሏል።
ሞዴሏ ፀጉሯን ለመቆረጥ ወደ ውበት ሳሎኑ የሄደችው እአአ በ2018 ነበር። በምን አይነት መንገድ ፀጉሯ እንዲስተካከል እንደምትፈልግ በዝርዝር አስረድታ ነበር።
ፀጉር አስተካካዮቹ ግን ፀጉሯን አራት ኢንች ብቻ አስቀርተው ቆረጡት።
የፍርድ ቤቱ መዝገብ እንደሚለው ግለሰቧ "ራሷን በመስታወት ማየት አቆመች። ከሰዎች ጋር መገናኘት የሚያስፈልገው ሥራ ነበራት። ነገር ግን ፀጉሯ በጣም በማጠሩ የተነሳ በራስ መተማመኗን አጣች።"
ለፀጉር ቤቱ ቅሬታዋን ስትናገር ስህተታቸውን ለማካካስ "ነጻ የፀጉር ቅባት እንስጥሽ" ነበር ያሏት። ይህ የፀጉር ቅባት ይባስ ብሎ ፀጉሯን አበላሽቶታል።
ሞዴሏ የአእምሮ መረበሽ ከገጠማት በኋላ መሥራት አልቻለችም። ገቢዋም ተቋርጧል። ላለፉት ሁለት ዓመታት ከፍተኛ የሕይወት መመሳቀል እንደገጠማትም በፍርድ ቤቱ ተነግሯል።












