በሕንድ ቀንደኛ ወንጀለኛ የነበረው ግለሰብ ፍርድ ቤት ውስጥ ተገደለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሕንድ ውስጥ በከባድ ወንጀሎች ተከሶ ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው ተጠርጣሪ ችሎት ውስጥ በተፈጸመበት ጥቃት መገደሉ ተዘገበ።
በአደገኛው የወንጀል ቡድን መሪ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው የተጠርጣሪው ጉዳይ በሚሰማበት ፍርድ ቤት ውስጥ ጠበቃ መስለው በቀረቡ ሁለት ሰዎች አማካይነት ነው።
በዋና ከተማዋ ዴልሂ ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመከታተል ችሎት የቀረበው የወንጀለኛ ቡድን መሪ የሆነው ጂቴንደር ማን ጎጊ ላይ በተፈጸመበት ጥቃት እዚያው ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ ገልጿል።
ባለሥልጣናት እንዳሉት ፖሊስ በጥቃት ፈጻሚዎቹ ላይ በከፈተው ተኩስ ሁለቱም የተገደሉ ሲሆን፤ ጥቃቱ በተፎካካሪ የወሮበሎች ቡድን አማካይነት የተፈጸመ ነው ሲል ጥርጣሬውን ገልጿል።
ችሎት ውስጥ የተገደለው የወንጀል ቡድን መሪው ጎጊ በዴልሂ ፖሊስ እጅግ ተፈላጊ ዝርዝር ውስጥ ከቀዳሚዎቹ አንዱ የነበረ ሲሆን፤ ፍርድ ቤት የቀረበው በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች ውስጥ በተፈጸሙ ግድያ፣ ጠላፋና ማጭበርበርን ጨምሮ በበርካታ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶበት ነው።
ይህ ፍርድ ቤት ውስጥ የተፈጸመው ግድያ በዋና ከተማዋ ዴልሂ ውስጥ በሚገኙ ችሎቶች ባለው የደኅንት ሁኔታ ላይ ጥያቄን አስነስቷል። አንድ ከፍተኛ ፖለቲከኛ በሰጡት አስተያየት ግድያው በደኅንነት ጥበቃው በኩል ከፍተኛ ችግር መኖሩን ያመለክታል ብለዋል።
ጎጊ በግድያና ገንዘብ በኃይል በመቀበል ክስ ምክንያት ከአንድ ዓመት በፊት ዴልሂ ውስጥ ተይዞ ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ነበር።
ባለሥልጣናት እንደሚሉት ጎጊ በወንጀሉ ዓለም በፍጥነት ስሙ እየገነነ በመምጣቱ በበርካታ የወንጀል ቡድኖች ኢላማ ውስጥ ገብቶ ነበር።
ስለግለሰቡ የወጡ ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት ገና ታዳጊ ሳለ በተለያዩ ወንጀሎች ውስጥ በመሳተፍ አደገኛውን ተግባር የጀመረ ሲሆን በተለይ በመኪና ጠለፋና በሌብነት ነበር የወንጀሉን ዓለም የተቀላቀለው።
በኋላ ላይ ግን በከባባድ ወንጀሎች ውስጥ በመሳተፍ ስሙ ይጠቀስ የነበረ ሲሆን፤ በተለይ ሃሪያና ግዛት ውስጥ የተገደለው ታዋቂ ዘፋኝን ጨምሮ በሌሎችም የታዋቂ ሰዎች ግድያ ውስጥ ዋነኛ ተጠርጣሪ ነበር።












