የአውሮፓ ሕብረት ሞባይል ስልኮች ተመሳሳይ የቻርጀር ገመድ እንዲኖራቸው ወሰነ

የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ስልክ አምራች ኩባንያዎች በሕብረቱ ውስጥ ለገበያ የሚቀርቡ ስልኮች ወጥ የሆነ 'የቻርጀር' ገመድ እንዲኖራቸው ወሰነ።
ሕብረቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ተጠቃሚዎች አዲስ ስልክ ሲገዙ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን 'ቻርጅር' በመጠቀም በአካባቢ ላይ የሚደርስ ብክለንት ለመቀነስ ነው።
በዚህ ውሳኔ መሠረትም በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ የሚሸጡ ስልኮች በሙሉ ዩኤስቢ-ሲ (USB-C) የተባለው የቻርጀር ገመድ አይነት ይኖራቸዋል ማለት ነው።
አፕል ኩባንያ መሰል ውሳኔ ፈጠራን ይጎዳል ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል። አፕል የሚያመርታቸው አይፎን ስልኮች "ላይትኒን" የተሰኙ ልዩ የሆኑ ቻርጅ ማድረጊያ ገመዶችን ይጠቀማሉ።
የአንድሮይድ ሥርዓትን የሚጠቀሙ እንደ ሳምሰንግ ያሉ አብዛኞቹ ስልኮች ዩኤስቢ ማይክሮ-ቢ (USB micro-B) የተሰኙትን ቻርጀር ይጠቀማሉ። የተወሰኑት ደግሞ ዩኤስቢ-ሲ (USB-C) የተሰኘውን ቻርጀር ይወስዳሉ።

የአፕል ምርት የሆኑ አይፓዶች እና ማክቡክ ኮምፒዩተሮች እንዲሁም በቅርቡ ለገበያ የቀረቡ ቅንጡ የሳምሰንግ እና ሁዋዌ ስልኮች ዩኢስቢ-ሲ ቻርጀር ገመድ ይቀበላሉ።
እስከ እአአ 2018 ድረስ በአውሮፓ ሕብረት ለገበያ ከቀረቡት ስልኮች መካከል ወደ ግማሽ የሚጠጉት ዩኤስቢ ማይክሮ-ቢ ቻርጀር ገመድ ያላቸው ሲሆን፣ 29 በመቶ የሚሆኑት ማይክሮ ሲ እንዲሁም 21 በመቶ ደግሞ ላይትኒንግ ቻርጀር ገመድ ነበራቸው።
ሕብረቱ ባስተላለፈው መመሪያ መሠረት ተንቀሳቃሽ ስልኮች፣ ታብሌቶች፣ ካሜራዎች፣ ማዳመጫዎች (ሄድፎንስ) እና ተንቀሳቃሽ ስፒከሮች ዩኢስቢ-ሲ ገመዶችን የሚጠቀሙ ይሆናል።
የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ውሳኔውን ተከትሎ ጥቅም ላይ ከማይውሉ የቻርጀር ገመዶች ጋር በተያየዘ በየዓመቱ ከ11ሺህ በላይ ቶን የሚወገድን ቆሻሻ ማስቀረት ይችላል ይላል።
ባለፈው ዓመት ብቻ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ ከ420 ሚሊዮን በላይ ስልኮችን ጨምሮ የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶች ለገበያ ቀርበዋል።
በአማካይ አንድ ሰው ሦስት የስልክ ቻርጀሮች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ መካከል ጥቅም ላይ የሚውሉት ሁለቱ ብቻ ናቸው ብሏል ሕብረቱ።
የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ውሳኔ ከ2022 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን አምራቾች በ24 ወራት ውስጥ መመሪያውን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል።












