ሉትዌኒያ ዜጎቿ ቻይና ሰራሽ ስልኮችን እንዲያስወግዱ አሳሰበች

የዢኦሚ ስልክ ማስታወቂያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሉትዌኒያ መከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ ዜጎች አዲስ ቻይና ሰራሽ ሞባይል ስልኮችን እንዳይገዙ፤ የገዙትንም እንዲያስወግዱ አሳሰቡ።

ምሥራቅ አውሮፓዊቷ አገር ሉትዌኒያ ቻይና ሰራሽ ስልኮች ተጠቃሚዎችን እንደሚሰልሉ እና የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው በጥናት አረጋግጫለሁ ብላለች።

የሉትዌኒያ ብሔራዊ የሳይበር ደኅንንት ማዕከል ሁዋዌ እና ዢኦሚ 5ጂ ስልኮች ችግር አለባቸው ብሏል።

ዢኦሚ ስልክ ስለላ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ተገጥሞለታል የተባለ ሲሆን ሁዋዌ ስልክ ደግሞ የደኅንነት ስጋት አለበት።

ዢኦሚ ኩባንያ ተጠቃሚዎቹን መሰለል የሚያስችል የተገጠመ ሥርዓት የለም ሲል ሁዋሄ በበኩሉ የስልኩ ደኅንነት የተረጋገጠ ነው ይላል።

"የእኛ ምክር ዜጎች ቻይና ሰራሽ ስልኮችን እንዳይገዙ እና የገዙትንም ስልክ በተቻለ ፍጥነት እንዲያስወግዱ ነው" በማለት የሉትዌኒያ መከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ ማርጊሪስ አቡኬቪሲአስ ተናግረዋል።

ዢኦሚ አሜአይ 10ቲ 5ጂ

ዢኦሚ የሚያመርተው አሜአይ 10ቲ 5ጂ ስልክ ቀድመው የተመረጡ ቃላትን እና ዓረፍተ-ነገሮችን እንዲለይ የሚያደርግ ሶፍትዌር ተገጥሞለታል ተብሏል።

"ነጻ ቲቤት"፣ "ታይዋን ነጻ ሆና ትኖራለች" እንዲሁም "ዲሞክራሲያዊ እንቅስቃሴ" የሚሉ መሰል 449 ዓረፍተ ነገሮችን እና ቃላቶችን ተጠቃሚው ሲያወጣ ስልኩ መዝግቦ ይይዛል ተብሏል።

ሉትዌኒያ አደረኩት ያለችው ጥናት ዢኦሚ ስልክ የሚሰበስባቸውን መረጃዎችን ሲንጋፖር ወዳለ ሰርቨር ሲልክ ቆይቷል ብሏል።

ዢኦሚ በበኩሉ የሚያመርታቸው ስልኮች በሙሉ የተጠቃሚውን ግላዊ መብት የሚያከብሩ ናቸው ይላል። የኩባንያው ቃል አቀባይ ስልኮቻቸው በፍጽም ተጠቃሚዎችን አይገድቡም፤ መረጃዎችንም ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው አይሰጡም ብለዋል።

ዢኦሚ በቅርብ ዓመታት የሚያመርታቸው ኪስን የማይጎዱ ስልኮቹ ከፍተኛ ሽያጭን እያስገኙለት ነው።

ሁዋዌ ፒ40

በሉትዌኒያ የተደረገው ጥናት የሁዋዌ ፒ40 5ጂ ስልኮች ለሳበር ደኅንነት ተጋላጭ ናቸው ብለዋል።

ለሁዋዌ ስልኮች መተግበሪያ የሚወርድበት አፕጋለሪ በቫይረስ ወደ ተጠቁ ሦስተኛ አካል መተግበሪ ማውረድ ወደሚቻልበት ገጽ ተጠቃሚዎችን ይልካል ብለዋል የሉትዌኒያ መካላከያ ሚኒስቴር እና ብሔራዊ የሳይበር ደኅንነት ማዕከል በጋራ ባወጡት መግለጫ።

የሁዋዌ ቃል አቀባይ በተመሳሳይ ለቢቢሲ በሰጠው ምላሽ በሉትዌኒያ የቀረበውን ክስ አጣጥል።

ቃል አቀባዩ ሁዋዌ በሚንቀሳቀስባቸው አገራት ሕግ እና መመሪያዎችን እንደሚያከብር እና የሳይበር ደኅንነት እና የተጠቃሚዎች ግላዊ መረጃዎች ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ሁዋዌ ተጠቃሚዎቹ ደኅንነታቸው የተረጋገጡ መተግበሪያዎችን ብቻ እንዲያወርዱም ኩባንያው የደኅንነት ማረጋገጫዎችን ያካሂዳል ብለዋል ቃል አቀባዩ።