ሮቦቲክስ፡ በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው የሮቦት ውድድር አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያዊ

ሰላሙ ይስሃቅ፤ በቤጂንግ በተካሄደው የሮቦት ውድድር አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያዊ

የፎቶው ባለመብት, Selamu Yisihak

በቻይና ቤይጂንግ በተካሄደ የሮቦት ውድድር በቲያንዢን ቴክኖሎጂ እና ኢጁኬሽን ዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆኑ አምስት ኢትዮጵያውያን የወርቅ፣ የብር እና የነሐስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

በውድድሩ የተሳተፉት ሰላሙ ይስሃቅ፣ አባኩማ ጌታቸው፣ ፀጋዬ አለሙ፣ ዮሐንስ ኃ/መስቀልና ሄኖክ ሰይፉ የተባሉ ኢትዮጵያውን ነበሩ።

ኢትዮጵያውያኑ በተወዳደሩበት ዘርፍ፣ ሰላሙ ይስሃቅ የወርቅ፣ አባኩማ ጌታቸው እና ፀጋዬ አለሙ የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል።

በተጨማሪም ዮሐንስ ኃ/መስቀል እና ሄኖክ ሰይፉ የነሐስ ሜዳሊያ እንዲሁም የዋንጫ ተሸላሚዎች ሆነዋል።

ቢቢሲ ያነጋገረው የወርቅ ተሸላሚው ሰላሙ ይስሃቅ ስለውድድሩ ሲያብራራ ኢትዮጵያውያኑ በትራይ ኮ ሮቦትስ ኤንድ አፕሊኬሽን ("Tri-Co" Robots and Robot Application) ዘርፍ መወዳደራቸውን ያስረዳል።

ውድድሩ ሦስት ሰዓታት የተሰጠው ነው። በእነነዚህ ሰዓታት ተነጣጥለው የተቀመጡና ግዑዝ የሆኑ አካላትን ገጣጥሞ 'ህይወት መዝራት'ና የሚሰጠውን ተልዕኮ የሚፈጽም ሮቦት ዝግጁ ማድረግ ደግሞ ውድድሩ ነው።

በቻይና ቤይጂንግ በተደረገው በዚህ ውድድር የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው ሰላሙ ይስሃቅ ይህንን ተግባር በአንድ ሰዓት ከ53 ደቂቃ በማጠናቀቅ አሸናፊ ሆኖ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል።

ከቀናት በፊት በተካሄደው በዚህ ውድድር ከ20 ዩኒቨርስቲዎች፣ የምርምርና የንግድ ተቋማት የተወጣጡ 2000 ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ሰላሙ ያሸነፈው በኢንደስትሪያል ሮቦቲክስና ሰው ሰራሽ ልህቀት ዘርፍ ነው።

በቤጂንግ በተካሄደው የሮቦት ውድድር አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያዊ

የፎቶው ባለመብት, Selamu Yisehak

ስለውድድሩ ምን ይታወቃል?

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 የተጀመረው ዓለም አቀፍ የሮቦት ኮንፈረንስ አካል የሆነው የሮቦትና የሰው ሰራሽ ልህቅ ውድድር በአራት ዘርፎች ይከናወናል።

በቻይና ቲያንጂን ግዛት በቲያንጂን ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው ሰላሙ ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ውድድር በኢንደስትሪያል ሮቦቲክስ ሥርዓት ዘርፍ ተወዳዳሪ ሲሆን በሌሎች ዘርፎች ከተሳተፉ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነው።

ሰላሙ የተሳተፈበት ውድድር "የተፈታታ" እና የኮፒውተር ፕሮግራም ያልተጫነበትን ሙሉ ሮቦት ገጣጥሞ ማዘጋጀት ነው።

ውድድሩ እያንዳንዱን ነገር በሚያስፈልግበት ቦታ አስቀምጦ [ሮቦቱ] የሚሰራ መሆኑን ማረጋገጥ ነው። እያንዳንዱን የሮቦት አካል ገጣጥሞ በዚያ ላይ ሶፍትዌር መጫን ሌላው የውድድሩ አካል ነው።

"አጋጣሚ ከቻይናዊ ጋር ነበር የተወዳደርኩት. . . በውድድሩ የሠራሁት ነገር በሙሉ በሚፈለገው ሁኔታ የሚሰራ መሆኑን ዳኞቹ አረጋግጠው ነው አሸናፊ መሆኔ ይተገለጸው" ሲል ያስረዳል።

ሮቦቱ "ሙሉ ለሙሉ በሚጠበቅበት ሁኔታ እንደሚሰራ፣ ከሌላ ቦታ ዕቃ እንዴት እንደሚያዟዙር፣ በታዘዘው መሰረት እንዴት ይንቀሳቀሳል የሚለውን በሙሉ ተፈትሿል። ይህንን ነው ሙሉ ለሙሉ የሰራነው።"

በቻይና ቤይጂንግ በተካሄደ የሮቦት ውድድር አምስት ኢትዮጵያውያን የወርቅ፣ የብር እና የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ መሆን ችለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Selamu Yisehak

የምስሉ መግለጫ, በቻይና ቤይጂንግ በተካሄደ የሮቦት ውድድር የተሳተፉት ሰላሙ ይስሃቅ፣ አባኩማ ጌታቸው፣ ጸጋዬ አለሙ፣ ዮሃንስ ሃ/ መስቀልና ሄኖክ ሰይፉ ከቻይናውያን ጋር

የኢንስትሪ ሮቦት ለኢትዮጵያ ምን ይጠቅማል?

ሰላሙ እያጠና ያለውን እና ያሸነፍበትን ኢንደስትሪያል ሮቦቲክስ አስፍላጊነትን ሲያስረዳ የቻይና እና የጀርመንን የመኪና ፋብሪካዎች በምሳሌነት ያስቀምጣል።

በእነዚህ አገራት መኪና ሲመረት "አብዛኛውን ነገር የሚገጣጥሙት ሮቦቶች ናቸው። ሰዎች መጨረሻ ላይ ውጤቱን እና ጤንነታቸውን ለማረጋገጥ ካልሄዱ በስተቀር ሙሉ ሥራውን ሮቦት ነው የሚከውነው" የሚለው ሰላሙ በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ ምርቶችን ለማቅረብ መሰል ቴክኖሎጂ አስፈላጊ መሆኑን ያነሳል።

"በኢትዮጵያ በቂ የሆነ በርካታ ጥሬ ዕቃ አለ። ያን ጥሬ ዕቃ እዚያው ፕሮሰሰ አድርገን ለዓለም ማቅረብ የምንችልበት ሂደት ላይ ግን ገና ነን። የሰለጠነ የሰው ኃይል ያስፈልገናል።"

እንደ ሰላሙ ገለጻ በአገር ውስጥ ያሉ ምርቶችን በዚህ የቴክኖሎጂ ሂደት እንዲያልፉ ማድረግ ከፍተኛ ጥቅም አለው።

ቡናን አብነት ያደርጋል "ኢትዮጵያ አንድ ኪሎ ቡና 200 ወይም 300 ብር ነው። እዚህ ግን የተዘጋጀ ግማሽ ኪሎ ቡና ስምንት መቶ የቻይና ገንዘብ ነው የሚሸጡት፤ በኢትዮጵያ ስምንት ሺህ ብር እንደማለት ነው። ኢትዮ ፍሌቨር ብለው ነው የሚሸጡት። ኢትዮጵያ ውስጥ ያ ቡና ተዘጋጅቶ ቀጥታ ወደ ቻይና ኤክስፖርት የሚደረግ ቢሆን የውጭ ምንዛሪ ገቢው ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል" ሲል ያስረዳል።

ከዚህም አልፎ እንደ ብረትና ሲሚንቶ ባሉ ፋብሪካዎች ኢንደስትሪያል ሮቦቲክስና ሰው ሰራሽ ልህቀትን ሥራ ላይ በማዋል በዝቅተኛ ወጪና ጉልበት ተወዳዳሪ ምርቶችን ማቅረብ ይችላልም ብሏል።

በቤጂንግ በተካሄደው የሮቦት ውድድር አሸናፊ የሆነው ኢትዮጵያዊ

የፎቶው ባለመብት, Selamu Yisehak

የሰላሙ ዕቅድ

ሰላሙ ይስሃቅ ወደ ቻይና ለትምህርት ከማቅናቱ ቀደም ብሎ በኢትዮጵያ ቴክኒካል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በመምህርነት ይሰራ ነበር።

እናም አሁን ትምህርቱን የሚከታተልበትና ቀድሞ ያስተምርት የነበረው ተቋም ኢንደስትሪያል ሮቦቲክስን ጨምሮ በአራት የትምህርት መስኮች በጋራ የመስራ ስምምነት ያላቸው በመሆኑ ወደ አገሩ ሲመለስ በዚሁ ዘርፍ ዜጎችን ለማፍራት ያልማል።

አራቱ የትምህርት መስኮች በቴክኒካል ዩኒቨርሲቲው በአንድ ማዕከል ስር የሚጠቃለሉ ሲሆን፣ ሰላሙና ሌሎች በቻይና በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉ ኢትዮጵያውን ወደ አገራቸው ተመልሰው በማዕከሉ በመሪ አሰልጣኝነት ይሰራሉ።

እንደ ሰላሙ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው ከሚሰጣቸው መደበኛ የትምህርት መርሃ ግብሮች በተጨማሪ የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎችን በመውሰድ ለዓለም አቀፍ የክህሎት ውድድር ዝግጅት እያደረጉ ነው።

በኢትዮጵያ ኢንደስትሪ እየተስፋፋ እንደሆነ የሚጠቅሰው ሰላሙ፣ ይህ ኢንድስትሪ ደግሞ በሰው ሰራሽ ልህቀት መታገዙ አይቀሬ ነው ይላል።

"ዓለም ወደ ዘመነበት አቅጣጫ ኢትዮጵያ እያደገች ነው ያለው። ለዚያ ደግሞ የተማረና ብቃቱ የተረጋገጠ ሰው ያስፈልጋል" እናም ይህን አይነት ሰው በአገሩ ውስጥ ለማብቃት እንደሚተጋ ገልጿል።