ቴክኖሎጂ ፡ ወደፊት በቪድዮ የሚደዋወሉ ሰዎች መጨባበጥ ይችሉ ይሆን?

በቪድዮ የሚደዋወሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'ዕድሜ' ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዙም የተባለው የቪድዮ መደዋወያ አውታር ሚሊዮን ዶላሮች ዝቋል።

ቫይረሱ ሰዎችን ከቤታቸው ሲከርችም የነበረው አማራጭ የቢሮ ሥራን ከቤት መከወን ነበር።

ስብሰባና ግምገማ ከሰፊው ጠረጴዛ ወደ 16 ኢንች ስክሪን ለመውረድ ተገደዋል።

የዚህ ዙም የተሰኘው ፍርቱና ያደለችው ቴክኖሎጂ መስራች እና ኃላፊ ደግሞ ግድየለም ወደፊት ተሰብሳቢዎች ቤታቸው ቁጭ ብለው ከስክሪኑ ወዲያኛው ጫፍ ያለውን ሰው እጅ መጨበጥ ይችላሉ እያለ ነው።

ምን እሱ ብቻ የቡና ሽታንም ከአንዱ ዓለም ወደ ሌላኛው በቴክኖሎጂ እገዛ አመጣለሁ ብሏል።

ኤሪክ ዩዋን ይህን ያለው በአንድ የድር ስብሰባ ላይ ነው።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ [ሰው ሰራሽ ልህቀት] የተሰኘውን ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ይህን ማድረግ አያቅተንም ይላል ዩዋን።

ሥራ አስኪያጁ ምንም እንኳ አሁን ሰዎች ቫይረሱን ቢላደሙትም ከቤታቸው ሆነው መሥራታቸውን ግን አያቆሙም የሚል ትንበያ አለው።

ሰውዬው ይህን ማለቱ ብዙም አያስገርምም። የቴክኖሎጂ ሰው ነውና።

ነገር ግን ፋይዘር የተሰኘው ክትባት አምራች ኮሮናቫይረስን እንደ መጋኛ የሚመታ ክትባት አግኝቻለሁ ካለ በኋላ የዙም የአክሲዮን ገበያ አሽቆልቁሏል።

ቢሆንም ዩዋን ሰዎች በሳምንት ለጥቂት ቀናት ወደ ቢሯቸው ያቀኑ ይሆናል እንጂ ከቤት ሆኖ መሥራት አዲሱ ባህላችን ይሆናል ሲል ይገምታል።

"ዓለም ከቤትና ከቢሮ ሆነን የምንሰራባት ትሆናለች። ይህን ደግሞ በፀጋ ልንቀበለው የሚገባ ነው" ባይ ነው ዩዋን።

"እመኑኝ እኔ እንኳን በቀን እስከ 19 ጊዜ የዙም ቪድዮ ስብሰባዎች አደርጋለሁ፤ ድካሜም ንሯል" ሲል የቪድዮ ስብሰባዎችን አሉታዊ ተፅዕኖ እነሆ ብሏል።

ኃላፊው በየቀኑ ለ15 ደቂቃ 'ሜዲቴት' እንደሚያደርግና ለነገ ምን አዲስ ነገር ይዤ ልምጣ የሚለውን እንደሚያሰላስል ለታዳሚዎች አሳብቋል።

በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ የቴክኖሎጂ ኩባንያው ሶስት ትሪሊዮን ደቂቃ የዙም ስብሰባ ይካሄዳል ብሎ ይገምታል።

ይህ ደግሞ ከዚህ በፊት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም።

ኩባንያው የተጠቃሚዎችን ደህንነትና ግለኝነት ሊጠብቅ ይገባል የሚል ቅሬታዎች ይነሱበታል።

ሰዎች 'ዙምቦምቢንግ' እያጋጠመን ነው ይላል። ነገሩ ወዲህ ነው። በጣም በርካታ ሰዎች በአንድ ጊዜ ይህን አውታር ሲጠቀሙ ቴክኖሎጂው ግራ ይጋባል። መቀባጠር ይጀምራል።

ነገር ግን "እኛ በቻልነው መጠን እየተመነደግን ነው" ይላል ዩዋን።

ዙም ከኮሮናቫይረስ በፊትም ነበረ። ከወረርሽኙ በፊት ግን ገና እምቦቃቅላ ነበር። ታዋቂነቱም ያን ያህል አልነበረም።

ኩባንያው በ2011 [በፈረንጆቹ] ሥራ ሲጀምር ኢንቨርሰተሮችን ማሳመን እጅግ ከባድ እንደነበር ዩዋን ይናገራል።

"ምን ያክል ጊዜ 'ወዲያ ሂድልን' የሚሉ መልዕክቶች እንደደረሱኝ ሁላ አላስታውሰውም - እጅግ በርካታ ነበሩ።" ብሏል።

ነገር ግን ሚያዚያ 2019 ላይ በኒው ዮርክ የአክሲዮን ገበያ ደወሉን አቃጭሎ ሥራውን ጀመረ።

በወቅቱ የቴክኖሎጂው የገበያ ዋጋ 9.2 ቢሊዮን ዶላር ነበር።

ሰውዬው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመምጣት 9 ጊዜ አመልክቶ 8 ጊዜ ተከልክሏል።

አልበገር ባይነቱ ለዚህ ስኬት እንዳበቃው ብዙዎች ይመሰክሩለታል።

ሰውዬው አሁን 18 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት እንዳለው ይገመታል። ነገር ግን በሕይወቱ ለውጥ መጥቷል ብሎ አያምንም።

"ዞር ብዬ ራሴን፣ ቤተሰቤን፣ ሥራዬን ስመለከት ይህን ያህል ለውጥ መጥቷል ብዬ አላስብም። ዙም ያው ዙም ነው። እኔም እኔ ነኝ - እንደውም ከዚህ በፊት ከምሠራው በላይ እየሠራሁ ነው።" ይላል።

""