ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ፡ በርካቶች ስብሰባ የሚያካሂዱበት ዙም ሚሊዮን ዶላሮች አተረፈ

ዙም

የፎቶው ባለመብት, ZOOM

በኮሮናቫይረስ ምክንያት በርካቶች ስብሰባ የሚያካሂዱበት ዙም በከፍተኛ ሁኔታ ትርፉ ጨመረ።

ድርጅቱ በሦስት ወራት 355 በመቶ ማለትም 663.5 ሚሊዮን ዶላር አትርፏል። ይህም ከተጠበቀው በላይ ነው።

የዙም ተጠቃሚዎች ቁጥር ከአምና ጋር ሲነጻጸር ወደ 458 በመቶ አድጓል።

የድርጅቱ ሼር ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጨምሮ 325.10 ዶላር ሆኗል። ዓመታዊ ገቢው ከ2.37 ቢሊዮን ዶላር እስከ 2.39 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል። ይህም ከተጠበቀው 30 በመቶ እጥፍ ነው።

ዙም ትርፋማነቱ እየጨመረ የመጣው በነፃ መተግበሪያውን ከሚጠቀሙ ሰዎች በተጨማሪ ገንዘብ የሚከፍሉ ትልልቅ ተቋሞችም ደንበኞቹ ስለሆኑ ነው።

ከ100 ሺህ ዶላር በላይ የሚያስገቡለት ተቋሞች ባለፉት ስድስት ወራት በእጥፍ አድገው 988 እንደደረሱ ድርጅቱ አስታውቋል።

በበይነ መረብ ስብሰባ ማካሄድ ከሚቻልባቸው መተግበሪያዎች መካከል ሲስኮ ዌቤክስ እና ማይክሮሶፍት ቲምስ ይጠቀሳሉ። የኮሮናቫይረስ ስርጭት መባባሱን ተከትሎ ትርፋቸው እየናረ ይገኛል።

ሆኖም ግን እንደ ዙም የተዋጣለት፣ ትርፉ የጨመረ፣ ዝነኛ የሆነም የለም።

በሌላ በኩል መረጃ ሰርሳሪዎችም መተግበሪያውን ኢላማ አድርገዋል።

ዙም የተጠቃሚዎችን መረጃ በሚስጥር እይዛለሁ ቢልም የግለሰቦችን መረጃ ለፌስቡክ እንደሚያስተላልፍ መረጃ ሰርሳሪዎች አጋልጠዋል።

ዙም፤ ስብሰባ የሚጠሩ ተቋሞች ወይም ሰዎች ተሰብሳቢዎችን እንዲከታተሉ እንደሚፈቅድም ተገልጿል።

ተቋሙ ከቻይና ጋር ባለው ቅርብ ትስስር ይተቻል። ወደ 700 ያህል ሠራተኞቹ ያሉት ቻይና ሲሆን፤ የአገሪቱ መንግሥት ሊጠቀምበት እንደሚችልም ስጋት አለ።