የሰዎችን ማንነት የሚለየው ቴክኖሎጂ እያከራከረ ነው

የ 'ፌስ ሪኮግኒሽን' ቴክኖሎጂ

የፎቶው ባለመብት, Amazon

በአንድ ምስል ወይም ቪድዮ ላይ ያሉ ሰዎችን ማንነት የሚለየው የ 'ፌስ ሪኮግኒሽን' ቴክኖሎጂ አሁንም እያከራከረ ነው።

አማዞን 'ሪኮግኒሽን' በሚል ስያሜ የሠራው የ 'ፌስ ሪኮግኒሽን' ቴክኖሎጂ ለአሜሪካ ፖሊሶች መሸጥ አለበት ወይስ የለበትም የሚለው ጉዳይ የአማዞን ባለድርሻዎች መካከል አለመግባባት ፈጥሯል።

ባለድርሻዎቹ በአማዞን ዓመታዊው ጉባኤ ላይ ምርጫ በማድረግ ውሳኔ እንደሚያሳልፉም ይጠበቃል።

ባለድርሻዎቹ፤ አማዞን 'ሪኮግኒሽን'ን ለመንግሥት ተቋማት መሸጥ አለበት? ቴክኖሎጂው የሰዎችን ሰብአዊ መብት ስላለመጋፋቱ በገለልተኛ ወገን ይጠና? የሚሉ ሁለት ጉዳዮች ላይ ምርጫ ያደርጋሉ።

አማዞን ምርጫው እንዳይካሄድ ለማድረግ ቢሞክርም የማስቆም መብት ስለሌለው አልተሳካለትም።

ሜሪ ቤት ጋልጋር የተባሉ ባለሙያ ለቢቢሲ፤ " 'ሪኮግኒሽን' ለመንግሥት ተቋሞች መስጠት የሚያስከትለው ተጽዕኖ ሳይጠና እንዳይሸጥ እንፈልጋለን። ውሳኔውን ለማሳለፍም ባለሀብቶች እንደሚያግዙን እናምናለን" ብለዋል።

ቴክኖሎጂው መቶ በመቶ ትክክለኛ መረጃ እንደማይሰጥ ጠቅሰው፤ ጥቅም ላይ ሲውል የሰዎችን መብት ተጋፍቶ እንደሚሰልል ተናግረዋል።

"ሰዎች፣ ፖሊሶች እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን እየተመለከቱና እየተከታሏቸው እንደሆነ ከተሰማቸው በነጻነት አይንቀሳቀሱም" ብለዋል።

አማዞን በበኩሉ 'ሪኮግኒሽን' ያለአግባብ ጥቅም ላይ ውሏል የሚል ሪፖርት ቀርቦ ስለማያውቅ ባለድርሻዎች እንዲደግፉት ጠይቋል።

ድርጅቱ በመግለጫው እንዳሳወቀው፤ ቴክኖሎጂው ወንጀለኞች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ያግዛል። "የጠፉ ሰዎች እንዲገኙ ይረዳል። ወንጀል መከላከልም ይቻላል። ያለአግባብ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል ብሎ አዲስ ቴክኖሎጂ ማጣጣል ተገቢ አይደለም" ተብሏል።

ወደ 20 ሚሊየን የሚጠጉ ሰዎች መረጃ ያለው ቴክኖሎጂው፤ በምስልና ቪድዮ ላይ የታየ ሰውን ማንነት ለማወቅ ያስችላል። የሰዎችን ጾታ ይለያል። ምስል ላይ ያለ ጽሁፍ እንዲተነተንም መረጃ ያቀብላል።

ሆኖም በኤም አይ ቲና ዩኒቨርስቲ ኦፍ ቶሮንቶ የተሠሩ ጥናቶች፤ ቴክኖሎጂው ሰዎችን በጾታቸውና በቆዳ ቀለማቸው የሚያገል መሆኑን ይጠቁማሉ። ቴክኖሎጂው የነጭ ወንዶችን ማንነት በቀላሉ ለማወቅ ቢረዳም ስለጥቁር ሴቶች ትክክለኛ መረጃ አይሰጥም።

አማዞን እነዚህ ጥናቶች የተሠሩት ቀድሞ በነበረው ቴክኖሎጂ እንደሆነና አሁን መሻሻሉን ይገልጻል። ቢሆንም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የአማዞን ሠራተኞችም ቴክኖሎጂውን ይቃወማሉ።