ወረርሽኙ መቀጠሉ የዙምን ሽያጭ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለፀ

የኮምፒውተር ስክሪን

የፎቶው ባለመብት, Zoom

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በርካታ የአለማችን ህዝብ በቤት መገደቡ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ለስብሰባዎችና ለሌሎች ዝግጅቶች መገልገያ የሆነው የድምፅና የቪዲዮው መተግበሪያው ዙም ከፍተኛ ሽያጭ እንዳስመዘገበና ትርፉም በዚሁም ሊቀጥልም እንደሚችል ኩባንያው አስታውቋል።

በካሊፎርኒያ መቀመጫውን ያደረገው የዙም ኩባንያ 2.5 ቢሊዮን ዶላርም ትርፍ አገኛለሁ ብሎ የተነበየ ሲሆን ይህም በመጋቢት ወር አገኘዋለሁ ብሎ ካሰበው እጥፍ ነው ተብሏል።

ወረርሽኙን ተከትሎም ስሙ የገነነው ዙም አገራት ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝን በማስተናገዳቸውም በርካታ ሰዎች ለየእለት ግንኙነታቸው ተመራጭ መተግበሪያ አድርጎታል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአለማችን ህዝቦችም መተግበሪያውን ከቤተሰብና ከጓደኞች ጋር ለመጫወት፣ በመማር ማስተማር ሂደት፣ ጉባኤዎችና የተለያዩ ዝግጅቶችን ለማካሄድና፣ ለስብሰባዎችም ተመራጭ አድርገውታል።

የዙም መስራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ ኤሪክ ዩዋን እንደሚሉት "ሰራተኞች ከየትኛውም ቦታ መስራትን በቀጠሉበት ወቅት" የከፋይ ኩባንያ ደንበኞች ቁጥር እየጨመረ ነው ብሏል።

በጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ ዙም 434 ሺህ ከአስር ሰራተኞች በላይ ያሉት ከፋይ ኩባንያ ደንበኞች እንዳሉት የተዘገበ ሲሆን ይህም ከባለፈው አመት ጋር 485 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው ተብሏል።

በዚህም ምክንያት ኩባንያው ከጠበቀው በላይ ሽያጭና ትርፍም እየተንበሸበሸ እንደሆነም ተነግሯል፥

ዙም ከባለፈው አመት ነሐሴ እስከ ጥቅምት ባለው የሩብ አመት ሽያጭ 777 ሚሊዮን ዶላር የመዘገበ ሲሆን ይህም ከሁለት አመት በፊት በዚህ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር 367 በመቶ ጭማሬ አሳይቷል።

ትርፉም በዚሁ ሩብ አመት 198.4 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን ከሁለት አመት በፊት የነበረው የሩብ አመት ትርፍ 2.2 ሚሊዮን ዶላር ነበር።

በዚህ ሳምንት ሰኞ ሽያጩንና ትርፉን እንደገና በመገምገም ለሶስተኛ ጊዜ አዲስ ትንበያን ያወጣ ሲሆን በመጪው አውሮፖውያኑ አዲስ አመትም 2.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚሆንም ለኢንቨስተሮች አሳውቋል።

በነሐሴ ወር ላይ ኩባንያው ተንብዮት የነበረው 2.37 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት የነበረው ሽያጭ 622̌.7 ሚሊዮን ዶላርም ነበር ተብሏል።