ቱርክ ውስጥ በደረሰ የጎርፍ አደጋ 31 ሰዎች መሞታቸው ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰሜናዊ ቱርክ ጥቁር ባሕር ዳርቻን ተከትሎ የተከሰተ የጎርፍ አደጋ 31 ሰዎችን ከገደለ በኋላ ከፍተኛ የነፈስ አድን ሥራ እየተከናወነ መሆኑ ተነገረ።
በጎርፍ አደጋው ክፉኛ የተመታው ካስታሞኑ የተባለው የቱርክ ግዛት ሲሆን 29 ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።
ቀሪዎቹ ሁለት ሰዎች ደግሞ በአደጋው የሞቱት ሲኖፕ በተባለ የባሕር ዳርቻ አካባቢ ነው።
ነፋስ በቀላቀለ ከባድ ዝናብ አማካይነት የተከሰተው ጎርፍ ሕንጻዎችንና ድልድዮችን ያፈረሰ ሲሆን መንገዶች በፍርስራሾችና በመኪኖች እንዲዘጉ አድርጓል። የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትም ተቋርጧል።
ቱርክ በዚህ ወር በደቡባዊ ግዛቷ ከባድ የሰደድ እሳት አጋጥሟት ነበር።
አሁን በቁጥጥር ስር መዋሉ የተነገረው ሰደድ እሳት ማርማሪስ በተባለው ግዛትና በዙሪያው ባሉ አካባቢዎች የነበሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችና ቱሪስቶችን ከስፋራው ለቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶጋን ትናንት አርብ በጎርፍ የተጎዳውን የካስታሞኑ ግዛትን ጎብኝተው በተወሰኑት ሟቾች የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።
ፕሬዝዳንቱ ለሟቾች በተደረገው የጸሎት ሥርዓት ላይ በታደሙበት ጊዜ "እንደ መንግሥት የምንችለውን አስፈላጊ የሆነውን ነገር በሙሉ በፍጥነት እናደርጋለን" ብለዋል።
"ያጣናቸውን ዜጎቻችንን መልሰን ልናመጣቸው አንችልም፤ ነገር ግን የቤተሰብ አባሎቻቸውን ላጡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማድረግ መንግሥታችን አቅሙና ሥልጣኑ አለው።" ሲሉ ተናግረዋል።
የፕሬዝዳንት ኤርዶጋን መንግሥት ቱርክ ውስጥ በቅርቡ ያጋጠሙ የተፈጥሮ አደጋዎችን በያዘበት መንገድ ላይ ትችት ሲሰነዘርበት ቆይቷል።
የጎርፍ አደጋው በተከሰተበት አካባቢ አደጋውን በመሸሽ በቤቶች ጣራ ላይ የነበሩ ሰዎችን በሔሊኮፕተሮች እንዲሁም ሌሎችን ደግሞ በጀልባዎች ለማዳን ተችሏል።
ከአደጋው ስፍራ ከ1,700 በላይ ሰዎች እንዲወጡ የተደረገ ሲሆን፤ በጎርፍ አደጋው ሳቢያ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያዎች ላይ ጉዳት በመድረሱ 330 የሚሆኑ መንደሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦባቸዋል።
ይህ በቱርክ የደረሰው የጎርፍ አደጋ ያጋጠመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም ላይ ሰዎች በሚያከናውኗቸው ተግባራት ሳቢያ ከባድ የተፈጥሮ አደጋዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ ያመለከተ ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ሳምንት ነው።
በቱርክ የጥቁር ባሕር ዳርቻ አካባቢ ያሉ ተራራማ ስፍራዎች በዚህ ወቅት ለጎርፍ አደጋ የተጋለጡ እንደሆነ ይነገራል።
ነገር ግን የቱርክ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሱሌይማን ሶይሉ የአደጋውን አካባቢ ሐሙስ ዕለት በጎበኙበት ጊዜ "ይህ ከዚህ ቀደም ካየኋቸው የጎርፍ አደጋዎች ሁሉ የከፋው ነው" ብለዋል።
በጎረቤት ግሪክ ያሉ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ባለፉት 48 ሰዓታት በጣሙን ሲፈለግ የነበረው ዝናብ እየጣለ በመሆኑ በአገሪቱ የተከሰተውን የሰደድ እሳት ለመቆጣጠር አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል።












