ቶክዮ ኦሎምፒክ፡ የሰሜን ኮሪያ ቴሌቪዥን የቶኪዮ ኦሊምፒክ ካለቀ በኋላ ውድድሮችን ማሳየት መጀመሩ እያነጋገረ ነው

ቶክዮ ኦሎምፒክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን የኦሊምፒክ ጨዋታዎች አልቀው የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት ተደርጎ ካበቃ ከሁለት ቀናት በኋላ እንደ አዲስ ውድድሮችን ማሳየት መጀመሩ እያነጋገረ ነው፡፡

የኮሪያ ሴንትራል ቴሌቪዥን በዩኬና በቺሌ መካከል የተደገውን እግር ኳስ ጨዋታ ለ70 ደቂቃ ለተመልካች አሳይቷል፡፡

ይህ ጨዋታ ተካሄዶ የነበረው ግን በጁላይ 21 ነበር፡፡

የሰሜን ኮሪያ ቴሌቪዥን ይህን ውድድር በምን ምክንያት ለሕዝብ ማሳየት እንደፈለገ፣ የውድድሩን ምሥልም ከየት እንዳገኘ የታወቀ ነገር የለም፡፡

ሰሜን ኮሪያ የኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንደተጀመሩ አካባቢ ለተወሰነ ጊዜ አንዳንድ ጨዋታዎችን ማሳየት ጀምራ ነበር፡፡ ሆኖም ባልታወቀ ምክንያት ሥርጭቱ ተቋርጧል፡፡

ባለፉት ዓመታት የእስያ ፓሲፊክ ብሮድካስቲንግ ኅብረት ለፒዮንግያንግ አንዳንድ ጨዋታዎችን እንድታሰራጭ ከደቡብ ኮሪያው ኤስቢኤስ ጋር በመተባበር በልዩ ሁኔታ ያቀርብላት ነበር፡፡

በዚህ ዓመት ግን የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ቴሌቪዥን የኦሊምፒክ ጨወታዎችን ፍቃድ ከየት አግኝቶ እንዳሰራጨ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

ሰሜን ኮሪያ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎችን ወደ ጃፓን አልላከችም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ አትሌቶቼ በኮቪድ ይያዙብኛል የሚል ነው፡፡

ፒዮንግያንግ አሁንም ድረስ ኮቪድ ተህዋሲ በአገሬ ዝር ብሎ አያውቅም ስትል ትከራከራለች፡፡ ሆኖም የኅብረተሰብ ጤና አዋቂዎች ይህ የማይመስል ነገር ነው ይላሉ፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት በነበረው የዊንተር ኦሊምፒክስ ሰሜን ኮሪያና ደቡብ ኮሪያ በጥምረት ተሳትፎ ማድረጋቸው አይዘነጋም፡፡ ያን ተከትሎም የሁለቱ አገሮች ዲፕሎማሲ ፈር እየያዘ መጥቶ ነበር፡፡

ያን ጊዜ ሰሜን ኮሪያ 22 ስፖርተኞችን ወደ ደቡብ ኮሪያ በመላክ በውድድሩ ስትሳተፍ ቡድኑን የመሩት ኪም ዮ ጆንግ ነበሩ፡፡ ዮ ጆንግ የአምባገነኑ የኪም ጆንግ ኡን እህት ናቸው፡፡

በዚህ ዓመት ሰሜን ኮሪያ ለኦሊምፒክ ተወዳዳሪ ሳትልክ ስትቀር ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ዘመን ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡