የቶኪዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ በመነከሱ ምክንያት በአዲስ ሊተካ ነው

የጃፓኗ ናጎያ ከተማ ከንቲባ ታካሺ ካዋሙራ

የፎቶው ባለመብት, KYOTO/REUTERS

የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዋ በትውልድ ከተማዋ ከንቲባ ሜዳሊያዋ በመነከሱ ምክንያት አዲስ ሊሰጣት ነው።

የጃፓኗ ናጎያ ከተማ ከንቲባ ታካሺ ካዋሙራ በአንድ ዝግጅት ላይ ጭምብላቸውን ዝቅ በማድረግ የሶፍትቦል ተወዳዳሪዋን ሚኡ ጎቶን ሜዳሊያ በመንከሳቸው በማኅበራዊ ድር አምባ ቁጣን ቀስቅሷል።

ከንቲባው የኮቪድ -19 ገደቦችን ችላ በማለት እና "አክብሮት የጎደለው" በሚል ተከሰዋል።

ይሁን እንጅ ከንቲባው ይቅርታ ከጠየቁ እና ለምትኩ ክፍያ እንደሚፈጽሙ ከተናገሩ በኋላ የኦሊምፒክ ባለሥልጣናት የጎቶ ሜዳልያ በአዲስ እንደሚለወጥ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት በሴቶች የሶፍትቦል የፍጻሜ ውድድር ጃፓን በአሜሪካን ላይ ድል አግኝታለች።

ከንቲባውም ይህን ድል ለማክበር ነበር ሜዳሊያውን በጥርሳቸው የያዙት፤ በኋላ ላይ ግን በድርጊታቸው ከመብጠልጠል አልዳኑም።

የማኅበራዊ ድር አምባ ተጠቃሚዎች ድርጊቱ ንጽሕና የጎደለው እና ለአትሌቷ ያሳዩት ጨዋነት የጎደለው ተግባር ነው ብለዋል።

"ለአትሌቶች የአክብሮት እጦት ከማሳየት ባሻገርም፤ አትሌቶች በሜዳልያ ሥነ ሥርዓቶች ወቅት ቫይረሱን ለመከላከል ሲባል ሜዳልያዎችን ራሳቸው ሲያጠልቁ ወይም ለሌሎች የቡድን አባላቶቻቸው ሲያጠልቁ ቢታዩም እሳቸው ግን ነክሰውታል። ይቅርታ፣ አልገባኝም!" ሲል የጃፓኑ የብር ሜዳልያ ተሸላሚ ዩኪ ኦታ በትዊተር ገጹ ላይ አስፍሯል።

በጃፓን በማኅበራዊ ድር አምባዎች ላይ "የጀርም ሜዳሊያ" የሚል ሃሳብ በስፋት እየተንሸራሸረ እየታየ ነበር።

ጎቶ የምትጫወትበት ቡድን ባለቤት የሆነው ቶዮታም ድርጊቱን "ተገቢ ያልሆነ" እና "እጅግ የሚያሳዝን" ብሎታል።

የ72 ዓመቱ ከንቲባ ለድርጊቱ በኋላ ላይ ይቅርታ ጠይቀዋል።

የከንቲባው ድርጊት ከ7,000 በላይ ቅሬታዎች ለከተማው ባለሥልጣናት እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል ተብሏል።

"እንደ ናጎያ አስተዳዳሪ ያለኝን ቦታ ረስቼ እጅግ ተገቢ ባልሆነ መንገድ እርምጃ ወስጄ ነበር' ሲሉ ለሚተካው ሜዳሊያ እንደሚከፍሉ ከንቲባው አስታውቀዋል።

የቶኪዮ 2020 አዘጋጆች ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ በአዲስ ሜዳሊያ በመተካቱ ዙሪያ በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ እና በጎቶ መካከል ከስምምነት ተደርሷል።

ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ወጪዎቹን ይሸፍናልም ብሏል።

ሜዳሊያዎችን መንከስ በውድድሮች ውስጥ የተለመደ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ ግን ይህን የሚያደርጉት አሸናፊዎቹ ብቻ ናቸው።

የቶኪዮ 2020 አዘጋጆች ባለፈው ሳምንት በትዊተር ገጻቸው ላይ "የ#ቶኪዮ2020 ሜዳሊያዎች የማይበሉ መሆናቸውን በይፋ ለመግለጽ እንፈልጋለን!" ሲሉ ጉዳዩን ወደ ቀልድ ወስደውት ነበር።

ካዋሙራም ሆኑ ጎቶ ግን በጉዳዩ ላይ ወዲያው አስተያየት አልሰጡም።