ሮሜሉ ሉካኩ፡ ቼልሲ ቤልጂየማዊውን አጥቂ ሪከርድ በሆነ በ97.5 ሚሊዮን ፓውንድ ከኢንተር ሚላን አስፈረመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቼልሲ አጥቂውን ሮሜሉ ሉካኩን ከኢንተር ሚላን በ97.5 ሚሊዮን ፓውንድ ከኢንተር ሚላን በድጋሚ አስፈረመ።
የ28 ዓመቱ ቤልጅየማዊ ከለንደኑ ክለብ እአአ በ2014 በ28 ሚሊዮን ፓውንድ ኤቨርተንን ቢቀላቀልም በድጋሚ በአምስት ዓመት ውል ስታምፎርድ ብሪጅ ደርሷል።
ክፍያው ማንችስተር ሲቲ ለጃክ ግሪሊሽ ከከፈለው የ100 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ክብረወሰን በጥቂቱ ያነሰ ነው።
ሉካኩ "ብዙ የመማር ችሎታ ያለው ልጅ ሆኜ መጥቼ ነበር። አሁን ብዙ ተሞክሮ እና በበለጠ ብስለት ተመልሻለሁ" ብሏል።
"ቼልሲን በልጅነቴ ደግፌያለሁ። አሁን ተመልሼ ብዙ ዋንጫዎችን እንዲያሸንፉ ለመርዳት መሞከር አስደናቂ ስሜት አለው።" ብሏል ሉካኩ።
ክለቦች ለሉካኩ የዝውውር ክፍያ 290 ሚሊዮን ፓውንድ ያህል በመክፈል በታሪክ ውስጥ ከማንኛውም ተጫዋች የበለጠ ብዙ ገንዘብ በአጥቂው ላይ አውጥተዋል።
በብሪታንያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ለአንድ ተጫዋች ከተከፈሉት አምስት ከፍተኛ ክፍያዎች መካከል ሁለቱ የሉካኩ ሆነዋል።
የቤልጂየም የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው በሴሪአ ክለብ የተሸጠ በጣም ውድ ተጫዋች ሲሆን በ2019 ከማንችስተር ዩናይትድ በ74 ሚሊዮን ፓውንድ፤ ጣሊያን የደረሰበት ዋጋ ደግሞ በሊጉ ሦስተኛው ከፍተኛ ዋጋ የወጣበት ተጫዋች ሆኗል።
በሊጉ የሚገኙ ክለቦች ከሌሎች ተጫዋቾች ጋርም ስማቸው እየተነሳ ይገኛል።
ማንቸስተር ሲቲ የ28 ዓመቱን እንግሊዛዊ አጥቂ ሃሪ ኬንን ከቶተንሃም ለማስፈረም 150 ሚሊየን ዩሮ ለመክፈል ተዘጋጅተዋል።
አጥቂው ፕሪሚየር ሊግ ጉዞው ከተጀመረ በኋላ የወደፊት ቡድኑ የበለጠ ግልፅ እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋል።
ሪያል ማድሪድ የ22 ዓመቱን ፈረንሳዊ አጥቂ ኪሊያን ምባፔን በ2022 ሲያስፈርም ፓሪስ ሴንት ዠርሜን በበኩሉ ከጁቬንቱስ የ36 ዓመቱን ፖርቹጋላዊ አጥቂ ክርስቲያኖ ሮናልዶን በማስፈረም ለመተካት ይፈልጋል።
ብራዚላዊው አማካይ ፊሊፔ ኩቲንሆ ከባርሴሎና ወደ ሊቨርፑል ይመለሳል ተብሎ ተጠብቋል። ብራዚላዊው ከመርሲሳይዱ ክለብ 142 ሚሊዮን ፓውንድ ወደ ስፔን ካመራ በኋላ ስሙ ከኤቨርተን፣ ማንቸስተር ዩናትድ፣ ቶተንሃም እና ሌስተር ጋር ሲነሳ ቆይቷል።
ሊቨርፑሎች ቤልጄማዊውን አጥቂ ጄረሚ ዶኩን ከሬኔስ ለማስፈረም ፍላጎት እንዳላቸው ተነግሯል። የ19 ዓመቱ አጥቂ 38 ሚሊዮን ፓውንድ ሊጠይቅ ይችላል።
የቀዮቹ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ግን ክለቡ "ብዙ ተጫዋቾችን አይፈልግም" ብለዋል።
ሪያል ማድሪድ እና ፓሪስ ሴንት ዠርሜይን የመሃል ተከላካዩ አንቶኒዮ ሩዲገር በቸልሲ ያለውን ሁኔታ እየተከታተሉ ሲሆን የቅድመ ኮንትራት ስምምነት በጥር ወር ከ28 ዓመቱ ጋር ሊፈራረሙ እንደሚችሉም ይታወቃል።
ቶተንሃሞች የቪያላሪያሉን የ24 ዓመት ስፔናዊ ተከላካይ ፓው ቶሬስን ሊያዘዋውሩ ይችላሉ።
ክሪስታል ፓላስ የሃድስፊልድ ታውንን እንግሊዛዊ አማካይ ሉዊስ ኦብራይን ለማስፈረም ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ለመፎካከር ተዘጋጅቷል።
የሳውዛምፕተን አሰልጣኝ ራልፍ ሃሰንሃትል በአስቶን ቪላ እና በቶተንሃም የሚፈለገውን የ26 ዓመቱን እንግሊዛዊ አማካይ ጀምስ ዋርድ-ፕሮስን ለማቆየት ቆርጠዋል።
ማንችስተር ዩናይትድ የአይቮሪኮስቱን አጥቂ አማድ ዲያሎን በውሰት ሊለቅ ነው።
ጁቬንቱስ አርሰናል በጥብቅ ሲፈልገው የነበረውን የ23 ዓመቱን አማካይ ማኑዌል ሎካቴሊን ከሳሱሎ ለማስፈረም ተዘጋጅቷል።
ዌስትሃም ለሞሮኮው ተከላካይ ናየፍ አጉየር ያቀረበው 17 ሚሊዮን ፓውንድ በሬንስ ውድቅ ተደርጎበታል።
ሊድስ ዩናይትድ የ24 ዓመቱን እንግሊዛዊ የፊት መስመር ተጫዋች ራያን ኬንትን ከሬጀርስ ለማስፈረም አዲስ ጥረት ሊያደርግ ይችላል።
የአርሰናሉ አሰልጣኝ ማይክል አርቴታ የዝውውር ቀነ -ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ተጨማሪ ተጫዋች የማስፈረም ተስፋ አላቸው።
የ32 ዓመቱ ስፔናዊ አጥቂ ዲዬጎ ኮስታ በታህሳስ ወር ከአትሌቲኮ ማድሪድ ከወጣ በኋላ አለመጫወቱን ተከትሎ ከአትሌቲኮ ሚኔሮ ጋር በብራዚል ሕይወቱን ሊጀምር እየተነጋገረ ነው።
የባርሴሎና የ32 ዓመቱ ብራዚላዊ ግብ ጠባቂ ኔቶ በዚህ ክረምት ወደ አርሰናል በቋሚነት ሊዛወር ይችላል። የውሰት ውልም ሊኖር ይቻላል ተብሏል።












