ኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት በኦሊምፒክ ዝቅተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው መቼ ነበር?

በ1984 ዓ.ም በተካሄደው የባርሴሎና ኦሊምፒክ ታሪክ የሰራችው ደራርቱ ቱሉ ከተፎካካሪዎቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ1984 ዓ.ም በተካሄደው የባርሴሎና ኦሊምፒክ ታሪክ የሰራችው ደራርቱ ቱሉ ከተፎካካሪዎቿ ጋር

በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአንድ ዓመት ተራዝሞ አምና ታቅዶ ዘንድሮ የተካሄደው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ውድድር ተጠናቋል።

ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የዘንድሮውን ውድድር በ113 ሜዳሊያዎች በቁንጮነት ስታጠናቅቅ፣ ቻይና ሁለተኛ፣ አዘጋጇ ጃፓን ሦስተኛ፣ ጎረቤት አገር ኬንያ 19ኛ፤ ኢትዮጵያ ደግሞ 56ኛ ሆነው አጠናቀዋል።

በዘንድሮው የኦሊምፒክ ውድድር ኢትዮጵያ ያመጣችው ውጤት ዝቅተኛ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ኢትዮጵያ ጎልታ ከምትታይባቸው ዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች መካከል ቀዳሚው በሆነው በኦሊምፒክ ውድድር ላይ የአገሪቱ አትሌቶች አኩሪ ውጤት እንዲያመጣ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በጉጉት ይጠብቃል።

በኦሊምፒክ መድረክ ላይ በባዶ እግሩ ጭምር ሮጦ በተከታታይ በማራቶን ወርቅ በማግኘት ታሪክ የሰራው አበበ ቢቂላ በተወዳደረባት ቶኪዮ በተካሄደው ኦሊምፒክ ላይ ኢትዮጵያ ከፍያለ ድል ታገኛለች ብለው ጠብቀው ነበር።

ነገር ግን የታሰበው ሳይሆን ልዑኩ ከመነሻው ባለመግባባት ውስጥ ሆኖ ኢትዮጵያ በዘንድሮው የኦሊምፒክ ጨዋታ 1 የወርቅ፣ አንድ የብር እና ሁለት የነሐስ በአጠቃላይ 4 ሜዳሊያዎች አግኝታ ባለፉት 20 ዓመታት ከተመዘገበው ዝቅተኛው ውጤት ሆኗል።

የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ብቸኛውን ወርቅ ማግኘት የቻለው በ10 ሺህ ሜትር በአትሌት ሰለሞን ባረጋ አማካይነት ነው።

በሦስት ሺህ ሜትር መሰናክል በአትሌት ግርማ ለሜቻ ብቸኛው ብር ሲገኝ ለተሰንበት ግደይና ጉዳፍ ፀጋይ እያንዳንዳቸው የነሐስ ሜዳሊያ አምጥተዋል።

የኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ቡድን በአትሌቲክስ 34 አትሌቶችን፣ በብስክሌት እሽቅድምድም አንዲት ሴት ተወዳዳሪ፣ በውሃ ዋና አንድ ተወዳዳሪ እንዲሁም በቴኳዋንዶ አንድ በድምሩ 37 ስፖርተኞችን ይዞ ነበር ወደ ቶኪዮ ያቀናው።

ኢትዮጵያ ባለፈው ብራዚል የሪዮ ላይ በተካሄደው የ2016 ኦሊምፒክ 1 የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ቢሆንም በሦስት የብርና 4 የነሐስ በድምሩ 8 ሜዳሊዎች ማግኘት ችላ ነበር።

በቶኪዮው ኦሊምፒክ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው ሰለሞን ባረጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቶኪዮው ኦሊምፒክ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው ሰለሞን ባረጋ

ኢትዮጵያ ባለፉት 20 ዓመታት

የዘንድሮው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጤት ባለፉት 20 ዓመታት ኢትዮጵያ ካስመዘገበቻቸው ውጤቶች ዝቅተኛው የሚባል ነው።

የዛሬ 20 ዓመት በተደረገው የሲድኒ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በአትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴና በሻለቃ ደራርቱ ቱሉ በ10 ሺህ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች እንዲሁም በሚሊዮን ወልዴና በገዛኸኝ አበራ 4 ወርቅ ማምጣቷ ይታወሳል።

ከዚህም በተጨማሪ በጌጤ ዋሚ፣ በአሰፋ መዝገቡና በተስፋዬ ቶላ አራት ሜዳሊያዎችን በማከል ውድድሩን በ8 ሜዳሊያዎች ነበር ያጠናቀቀችው።

ከሲድኒ ቀጥሎ የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን ባዘጋጀችው የግሪኳ አቴንስም ኢትዮጵያ በአትሌቶቿ በሜዳሊያ ተንቆጥቁጣ ነበር።

ኢትዮጵያን ወክሎ ወደ ግሪክ መዲና አቴንስ ያቀናው የኦሊምፒክ ቡድን በቀነኒሳ በቀለና በመሠረት ደፋር ሁለት ወርቆችና በሌሎች አትሌቶች ደግሞ ተጨማሪ 5 ሜዳሊያዎች በድምሩ 7 ሜዳሊያዎች ይዞ ተመልሷል።

የውድድሩን አዘጋጅነት ከአቴንስ የተረከበችው የቻይናዋ ቤይጂንግም የኢትዮጵያ ባንዲራ ከፍ ብሎ መውለብለቡ ከአእምሮ የሚጠፋ አይደለም።

በወቅቱ የቤይጂንግ ኦሊምፒክ ፈርጦች የተባሉት ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ እያንዳንዳቸው በ10 ሺህና 5 ሺህ ሜትር ውድድሮች ሁለት ሁለት ወርቅ በማምጣት ደምቀው ነበር።

ከጥሩነሽና ቀነኒሳ በተጨማሪ በመሠረት ደፋር፣ በስለሺ ስህንና በፀጋዬ ከበደ ሜዳሊያዎች ታጅቦ ነው ቡድኑ አዲስ አበባ የገባው።

በፈረንጆቹ 2012 በተካሄደው የለንደን ኦሊምፒክ ላይም ኢትዮጵያ ሜዳሊያ ብርቋ አልነበረም።

በዚህ ውድድር ሦስቱ እንስት አትሌቶች ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋርና ቲኪ ገላና ወርቅ ማጥለቃቸው ይታወሳል።

በለንደን ኦሊምፒክ ከሦስቱ አትሌቶች በተጨማሪ ሁለት ብርና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን በአትሌቶቿ ያገኘችው ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ የተመለሰችው በደመቀ ድል ነበር።

በሪዮው ኦሊምፒክ ደግሞ አንድ ወርቅ፣ ሁለት ብርና 5 ነሐስ በማምጣት 8 ሜዳሊያዎችን ለማግኘት ችላ ነበር።

የዘንድሮው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጤት ባለፉት 20 ዓመታት ኢትዮጵያ ከተመዘገበው የሜዳሊያ ብዛት ዝቅተኛው ነው።

ሻምበል አበበ በቂላ መስከረም 11 1960 ሮም

የፎቶው ባለመብት, Keystone-France

ቅድመ - 2000

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ውድድሮች መሳተፍ የጀመረችው ከፈረንጆቹ 1956 ጀምሮ ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1956ቱ አውስትራሊያ ውስጥ በተካሄደው የሜልበርን ኦሊምፒክ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በውድድሩ ሜዳሊያ ማግኘት ሳይችል ተመልሷል።

ነገር ግን በተከታይነት በተካሄደውና ኢትየጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በተሳተፈችበት የሮም ኦሊምፒክ የመጀመሪያውን ሜዳሊያ በአበበ ቢቂላ አማካይነት ለማግኘት ችላለች።

ኢትዮጵያ በ1976 በካናዳው የሞንትሪያል ኦሊምፒክ ጨዋታዎች እንዲሁም በተከታታይ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስና በደቡብ ኮሪያዋ ሴኡል በተካሄዱት ኦሊምፒኮች አልተሳተፈችም።

ነገር ግን በፈረንጆቹ 1980 ሞስኮ ላይ በተካሄደው ኦሊምፒክ ተሳትፋ በሁለት የወርቅና በሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች ከዓለም 17ኛ መውጣት ችላለች።

ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ አንስቶ እስከዛሬ ድረስ በተሳተፈችባቸው የኦሊምፒክ ውድድሮች በአትሌቲክስ 55 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች።

ይህ ውጤት ኢትዮጵያን ከኬንያና ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል በአፍሪካ በርካታ የኦሊምፒክ ሜዳሊያ ያላት ሦስተኛዋ አገር ያደርጋታል።

በዘንድሮው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ደግሞ በሜዳሊያ ብዛት ከአፍሪካ አምስተኛ መሆን ችላለች።

የአፍሪካ ሜዳሊያ