የጋዳፊ ልጅ ከሩስያው ቅጥረኛ ተዋጊ ጋር ግንኙነት አለው በሚል የእስር ትዕዛዝ ወጣበት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሊቢያ ዓቃብያነ ሕግ ከሩስያ ቅጥረኛ ተዋጊ ጋር ግንኙነት አለው በሚል የሟቹ የሊቢያው መሪ የሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ ላይ የእስር ማዘዣ አውጥተዋል።
ቢቢሲ በሰራው የጋዜጠኝነት ምርመራ ዋግነር የሚባልና ባለቤትነቱም ከአንድ ሩሲያዊ ባለሃብት ጋር የሚገናኝ ቅጥረኛ የጦር ተዋጊ ኩባንያ በሊቢያ ጦርነት መሳተፉን ነው።
ይህ ኩባንያ በሊቢያ ዜጎች ላይ የተፈፀሙ የጦር ወንጀሎች መካከል ግንኙነት እንዳለውም የምርመራ ዘገባው አጋልጧል።
የሩሲያ ተዋጊዎች በሊቢያ መጀመሪያ የታዩት ከሁለት አመታት በፊት ሲሆን ይህም የአማፂው ጄኔራል ካሊፋ ሃፍታር ጦርን ተቀላቅለው በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው መንግሥት ላይም በመዲናዋ ትሪፖሊ ጥቃት ሰንዝረዋል።
ግጭቱም በዘንድሮው አመት ጥቅምት ወር በተኩስ አቁም ተጠናቋል።
የዋግነር ቡድን ለመጀመሪያ ጊዜ የታወቀው በአውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን በወቅቱም በምስራቅ ዩክሬት በተነሳው ግጭት ለሩሲያ ደጋፊ ተገንጣዮች ድጋፍ በሰጡበት ወቅት ነው።
የሰይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተሰጠው ትዕዛዝ በአቃቤ ህጉ መሐመድ ጋውሮዳ አማካኝነት ከቀናት በፊት በሊቢያ የደህንነት አካላት ውስጥ እንዲሰራጭ ተደርጓል። ነገር ግን የቢቢሲ የምርመራ ዘገባን ተከትሎ ይፋ ሆኗል።
ሰይፍ አል-ኢስላም ጋዳፊ ማን ነው?
ሰይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት እንዳለው ሲጠረጠር ቆይቷል።
በሊቢያ በአውሮፓውያኑ 2011 ከተነሳው አመፅ በፊት ለውጥን ያመጣል የሚል ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
አባቱ ሙዓመር ጋዳፊ አገሪቷን ከ1969 በኃይል እስከተገረሰሱበት ወቅት ድረስ ሊቢያን ገዝተዋል።
በታዋቂው የለንደን ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የተማረ አንደበተ ርቱዕ፣ በአገሪቱ ውስጥ በጣም ተደማጭ ከሆኑ ሰዎች አንዱ እና አባቱንም ይተካል የሚል ተስፋም ነበር።












