ጃል መሮ፡ ከህወሓት ጋር ስለተደረገው ወታደራዊ ስምምነት ኩምሳ ድሪባ ምን ይላል?

መሮ

የፎቶው ባለመብት, ማህበራዊ ሚዲያ

መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጃቸው ህወሓትና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን ከኢትዮጵያ መንግሥት አንጻር በወታደራዊ መስክ ለመተባበር መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

በሁለቱ ቡድኖች መካከል ቀደም ሲል ከነበረው ጠላትነት አንጻር የሚኖራቸው መተማመን "ጊዜ የሚፈታውና የሚገልጠው ነገር ነው" ሲል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪ ኩምሳ ድሪባ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ኦነግ-ሸኔ በሚል መንግሥት የሚጠራው ቡድንን ቀደም ሲል በምዕራብ ኃይል አዛዥ የነበረውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአጠቃላዩ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪ እንደሆነ የሚነገረው ኩምሳ ድሪባ ወይም መሮ ለቢቢሲ "ሁለቱም ቡድኖች የጋራ ጠላት ስላለን በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ለመደጋገፍ ከስምምነት ላይ ደርሰናል" ብሏል።

በተለይ በምዕራብ የኦሮሚያ ክፍል ውስጥ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሰላማዊ ሰዎች እና በመንግሥት ኃላፊዎች ላይ በሚፈጸሙ ግድያዎች መንግሥት ቡድኑን ተጠያቂ ሲያደርገው የቆየ ሲሆን ከህወሓት ጋር አብሮ እንደሚሰራም በተደጋጋሚ ሲገለጽ ነበር።

ነገር ግን ይህ ቡድን ሲሰነዘሩበት የቆየውን ክሶች ሲያስተባብል የቆየ ሲሆን ከህወሓት ጋርም ግንኙነት እንደሌለው ሲገልጽ ቆይቷል።

የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የሽግግር መንግሥት ካቋቋሙት ኃይሎች መካከል አንዱ የነበረው ኦነግ በኢህአዴግ በተፈጸመበት ፖለቲካዊና ወታደረዊ ጫና ከፖለቲካዊ መድረኩ ተገፍቶ በመውጣት መሪዎቹ ለበርካታ ዓመታት በስደት ሆነው የትጥቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል።

ኩምሳ ድሪባም ቡድኑ ቀደም ሲል ከህወሓት ጋር ስለነበረው ግንኙነት ለቢቢሲ ሲናገር "የኦሮሞ ሕዝብ ከህወሓት ጋር የነበረው ግንኙነት ግልጽ ነው። ህወሓት በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ መስዋዕትነት ሕዝቡ ከፍሏል" ብሏል።

"ነገር ግን በተከፈለው መስዋዕትነት ህወሓት ከሥልጣን ተወግዶ ለውጥ ከመጣ በኋላ በኋላም ታይቶ በማይታወቅ አይነት ሌላ የከፋ መስዋዕትነት የሚያስከፍልና ማንነቱን ዝቅ የሚያደርግ ሁኔታ" ገጥሞታል ሲል ተናግሯል።

በዚህም ምክንያት ነው የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከህወሓት ጋር በወታደራዊው መስክ በትብብር ለመስራት ከስምምነት መድረሱን አመልክቷል።

ኩምሳ ድሪባ የሚመራው ኃይል ከህወሓት ጋር በመቀናጀት ጥቃቶችን እንደሚፈጽምና የተለያዩ ድጋፎችን ያገኛልመባሉንም አስመልክቶ ቢቢሲ ከአንድ ዓመት በፊት ጠይቆት በሰጠው ምላሽ ይህንኑ አስተባብሎ ነበር።

በወቅቱም "የኦሮሞን ሕዝብ ትግል ከሚደግፉ ማናቸውም አካላት ጋር አብረን ልንሰራ እንችላለን። ይህ መብታችን ነው። ለምን ሰይጣን አይሆንም። ኦሮሞን ነጻ የሚያወጣ ከሆነ አብረነው ልንሰራ እንችላለን። ይሁን እንጂ እንደሚባለው ከህወሓት ጋር አብረን ልንሰራ አንችልም። ብዙ ጠባሳ ስላለብን ከህወሓት ጋር ፈጽሞ ልንሰራ አንችልም" ብሎ ነበር።

የቡድኑን የአቋም ለውጥ በተመለከተም "እዚህ ውሳኔ ላይ መድረስ ቀላል አልነበረም። የኦሮሞ ሕዝብ ቁስል አለው ስለዚህም ጊዜ ወስደን ተወያይተንበት ችግር መፍታት በሚችል መልኩ እና የኦሮሞ ሕዝብን ጥቅም በማያስነካ ሁኔታ ከህወሓት ጋር ያለንን የጋራ ጠላት ለመጣል በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ተስማምተናል" ብሏል።

በተለያዩ ጊዜያት ቡድኑ ከህወሓት ጋር የቀረበ ግንኙነት እንዳለው በመንግሥት በኩል ሲነሳ የቆየ ሲሆን በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ውስጥ በተደጋጋሚ በሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ሁለቱ ቡድኖችን መንግሥት ተጠያቂ ሲያደርግ ነበር።

ይህንንም በተመለከተ የተጠየቀው ኩምሳ ድሪባ ቡድኑ ከዚህ በፊት ከህወሓት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልነበረው ተናግሮ፤ "አሁንም ከእነሱ ምንም የሚፈልገው ድጋፍ የለም ወደፊትም ሊኖር አይችልም" ብሏል።

"ነግር ግን ፖለቲካ ውስጥ ጨዋታ አለ። ፖለቲካ ውስጥ ቂም የማይቋጠርበት ጊዜ አለ። ቋሚ ጠላትም ሆነ ወዳጅ የለም። ጊዜውን ማየትና ከጊዜው ጋር መራምድ ይጠይቃል" በማለት አሁን ከህወሓት ጋር ለመተባበር የደረሱትን ስምምነት መነሻ ገልጿል።

በዚህ ሁኔታ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ምን ያህል መተማመን ሊኖር ይችላል የሚል ጥያቄ ከቢቢሲ የቀረበለት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪ መሮ "ይህ ጊዜ የሚፈታውና የሚገልጠው ነገር ነው" ብሏል።

ጨምሮም አሁን ያለው ጊዜ በህወሓትና በኦነግ መካከል መካረርና ጠላትነት ውስጥ ከተገባበት 1980ዎቹ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል የሚለው ኩምሳ "አሁን ያለው የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ ንቃት በዚያ ወቅት ከነበረው ይለያል። ህወሓትም እያደረገ ያለው ትግል ከዚያ ጊዜ የተለያየ ነው" ሲል ጠቅሷል።

ስለዚህ የሁለቱን ቡድኖች ትብብርና ግንኙነት "ጊዜ የሚፈታው ነገር ቢሆንም አሁን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ከሩቁ ሆኖ ከማየት ተቀራርበን ብንሰራ ብለን ነው ወሰንነው" ሲል ተናግሯል።

"ስምምነታችን ወታደራዊ ነው እነሱ ትግራይ ውስጥ እኛ ኦሮሚያ ውስጥ በመሆን ለመተባበር ነው የተስማማነው" የሚለው ኩምሳ

ሁለቱ ቡድኖች በአሁኑ ወቅት ደረስን ያሉት ስምምነት ላይ ለመድረስ ለአንድ ወር ያህል ሲነጋገሩ መቆየታቸውን የገለጸ ሲሆን፤ ይህ ወታደራዊ ትብብር ወደፊት ወደ ፖለቲካዊ አጋርነት እንዲያድግ ውይይት እየተደረገ መሆኑንም አመልክቷል።

ወታደራዊው ስምምነት ምን ምን እንደሚያካትት በዝርዝር ያልተገለጸ ሲሆን ከዚህ በፊት መንግሥት ህወሓት ኦነግ-ሸኔን በስልጠናና በመሳሪያ ያግዘዋል የሚለው በተመለከተም "ይህ ውሸት ነው ዛሬ እራሱ ከተባለው ደረጃ ላይ አልደረስንም" በማለት አስተባብሏል።

ያሉ ጥያቄዎችንና ችግሮችን በሰላማዊ የንግግር መድረክ ለመፍታት ቡድኑ ያለውን ፍላጎት በተመለከተ የተጠየቀው ኩምሳ ድሪባ "የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም በሚያስከብር መክኩ የሚደረግ ሰላማዊ ንግግርን እንቀበላለን። ነገር ግን ጊዜው ያለፈበት ይመስላል መንግሥትም ለዚህ ፍላጎት ያለው አይመስለኝም" ብሏል።

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች እናደርገዋለን የሚሉት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ቀጣይ ግብን በተመለከተም የኦሮሞ ሕዝብ ከጭቆና ወጥቶ የእራሱን እጣ ፈንታ እንዲወስን ለማድረግ መሆኑን ገልጿል።

ከሮይተርስ ዜና ወኪል ጋር በሳተላይት ስልክ የተናጋገሩት የህወሃት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል ከቡድኑ ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ቢያረጋግጡም ተጨማሪ ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።

የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት ጌታቸው ረዳም እንዲሁ "አንዳች አይነት ስምምነት" ላይ ለመድረስ ሥራዎች እየተሰሩ ነበር ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል።

ጨምረውም "በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ላይ ድርሻ ካላቸው ወገኖች ጋር በጋራ መሥራት ምንም አዲስ ነገር የለውም" ሲሉ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢለኔ ስዩም ሁለቱን ቡድኖች በተመለከተ በኢሜል በሰጡት ምላሽ ህወሓት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በአገሪቱ ፓርላማ ሽብርተኛ ድርጅቶች መሆናቸውን ከመጥቀስ ውጪ ዝርዝር እንዳልሰጡት ለሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።

ሁለቱ ቡድኖች በተለያዩ ስፍራዎች ከተፈጸሙ ጥቃቶችን በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር በተያያዘ በመንግሥት ክስ ሲቀርብባቸው የቆዩ ሲሆን በሚያዝያ ወር ማብቂያ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ድርጅቶች ብሎ እንደሰየማቸው አይዘነጋም።

ይህ የህወሓትና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወታደራዊ ስምምነት መደረሱ ይፋ ከተደረገ በኋላ በማኅበራዊ የትስስር መድረኮች ድጋፍና ተቃውሞዎች እየተሰሙ ነው።

ህወሓት ከሦስት ዓመት በፊት የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ በተካሄደ የለውጥ ሂደት ከማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ የነበረውን ቁልፍ ሚና በማጣት መቀመጫውን ትግራይ አድርጎ ቆይቶ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብቷል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለረጅም ዓመታት መቀመጫውን በኤርትራ አድርጎ የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የቆየውና ከለውጡ በኋላ በሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ ለመንቀሳቀስ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰው ኦነግ የተገነጠለ ታጣቂ ቡድን ነው።