የአምነስቲ ሪፖርት በተሳሳተ ዘዴ ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መንግሥት ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለወራት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ የተፈፀሙ ወሲባዊ ጥቃቶችን የዳሰሰበት የጥናት ውጤት ይፋ መደረጉን ተከትሎ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርቱ በተሳሳተ ዘዴ ላይ የተመሰረተ ነው ሲል ተቸ።
የአምነስቲ ሪፖርት በተሳሳተ ዘዴ ላይ የተመሠረተ እና በሱዳን ስደተኞች መጠለያ ካምፖች ውስጥ በተካሄዱ ቃለ ምልልሶች እና የማኅበረሰብ ሠራተኞች ባቀረቡት የርቀት ቃለ -መጠይቆች ላይ የተመሠረተ ነው ሲልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ሪፖርቱ ላይ ጥያቄ አንስቷል።
አምነስቲ 39 ገፆች በያዘው ሪፖርቱ የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም የአማራ ኃይሎች አስገድዶ የመድፈርን ጥቃትን እንዲሁም የወሲብ ባርነትና መታገት ጭምር እንደፈፀሙ አካትቷል።
አምነስቲ ከተለያዩ የጤና ተቋማት ሰበሰብኩት ባለው መረጃ መሰረት ከየካቲት እስከ ሚያዝያ ባሉት ወራት ብቻ በጦርነቱ 1288 የሚሆኑ የመደፈር ጥቃት ሰለባዎች ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት ሄደው ሪፖርት እንዳደረጉ ጠቅሷል።
ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው 68 የጥቃቱ ሰለባዎች መካከል አብዛኛዎቹ ወደ ጤና ተቋም አለመሄዳቸውን በመጥቀስ ወደ ሕክምና ተቋማት የሄዱ ሰዎች ቁጥር የጥቃቱን ስፋት አያሳይም ሲል አምነስቲ ጠቅሷል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በመግለጫው ላይ አምነስቲ መረጃ ለመሰብሰብ ተጠቀምኩባቸው ያላቸውን የማኅበረሰብ ሠራተኞች ማንነት ላይ ጥያቄ አለኝ ብሏል።
መግለጫው አሸባሪ ብሎ የጠራውን የህወሓት ኃይል አሰራር ለተረዳ በሙሉ የእነዚህ የማኅበረሰብ ሠራተኞች ማንንት ታላቅ ሚስጥር አይደለም ብሏል።
በተጨማሪም አምነስቲ 63 ግለሰቦችን ቃለ ምልልስ ካደረገ በኋላ ባደረገው በውስን እና የርቀት ምርመራ ሊደገፍ በማይችል መልኩ ጥልቅ ወደሆነ መደምደሚያ ደርሷል ብሎታል።
ቃለ መጠይቆቹም እየተካሄዱ ያሉት በሱዳን ውስጥ ባሉ የስደተኞች ካምፖች ውስጥ በማይካድራው ጭፍጨፋ የተሳተፉ እና በርካታ የህወሓት ሚሊሻዎች በሰፈሩበት ቦታ ነው ብሏል።
ከፍተኛ የመንግሥት አካል የወሲብ ጥቃትን ታግሷል የሚሉ ክሶችን ጨምሮ የሪፖርቱ መደምደሚያዎችን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የአምነስቲ ምርመራው በቂ ያልሆነና የጉድለት ያለበት ይመስላል ብሏል።
ከዚህ ቀደምም ቀደም ባሉት አንዳንድ ሪፖርቶች ውስጥ አምነስቲ "ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ ጥቃቶች እና በመንግሥት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻዎችን ለማድረግ የወሰነ ይመስላል" ብሎታል መግለጫው።
ከዚህ በተጨማሪም በአምነስቲ ምሥራቅ አፍሪካ ጽህፈት ቤት ውስጥ ስላሉ አንዳንድ ሠራተኞች ገለልተኛነት እና ሙያዊነት መንግሥት ስጋቱን ቀድሞውኑ ገልጾ እንደነበር አስታውሶ የአሁኑ ዘገባ እነዚያን ስጋቶች የሚያጠናክር ነው ብሏል።
የአምነስቲ ሪፖርቱ በተባበሩት መንግሥታት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ በጋራ ለሚያደርጉት ምርመራ ዕውቅና አለመስጠቱ አስገራሚ ነው ብሏል።
ይልቁንም የአምነስቲ ሪፖርቱ በሰጠው ምክር የተባበሩት መንግሥታት አካላት የሆኑት የፀጥታው ምክር ቤት እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት ምርመራ አካሂደው ጥፋተኞች ለሕግ እንዲቀርቡ ጥሪውን አቅርቧል።
እነዚህ ምክሮች በተለያዩ ፍላጎቶች ለመታዘዝ ፈቃደኛ ባልሆኑ አገሮች ውስጥ የሰብአዊ መብቶችን መሣሪያ ለማድረግ የሚሞክሩ ናቸው ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በግጭት ወቅትም ይሁን በማንኛውም ሁኔታ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶችን እንደሚያወግዝና ይህንንም የሚታገስበት ሁኔታ እንደሌለም አስታውሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ባለው ግጭት የተወሰኑ የሠራዊቱ አባላት ከተሰጣቸው መመሪያና ሕግ በመውጣት ፆታዊ ጥቃት ማድረሳቸውን አምኗል።
ወሲባዊ ጥቃቶችንም ሆነ ሌሎች ሕገወጥ ተግባራትን ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱንና ወሲባዊ ጥቃት የፈፀሙ አካላት ፍትህ ቦታ እስኪቀርቡ ድረስ እርምጃው እንደሚቀጥልም አፅንኦት ሰጥቶታል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ወሲባዊ ጥቃት የሚያስከትለውን አካላዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ጫናን በመረዳትም ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመጣመር ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሷል።
በዚህ ግጭት በሚያሳዝን ድርጊት ተጠቂ ለሆኑትም የሥነ ልቦናና የማማከር አገልግሎት ሥራዎች እየተሰጡ ነበር በማለትም ገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በግጭቱ ወቅት ደረሱ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን መቋቋሙን አስታውቆ ነበር።
ጾታዊ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ የሠራዊት አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ጠቅላይ ሚንሰትሩ ከዚህ ቀደም ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ የአምነስቲ የምሥራቅ አፍሪካ አጥኚ የሆኑት ፍስሃ ተክሌ በቁጥጥር ሥር ዋሉ የተባሉት ሰዎች ቁጥር ከደረሰው ጉዳት ስፋት ጋር የማይነጻጸር ነው ይላሉ።
አክለውም "የጾታዊ ጥቃቶች ፍርድ ሂደት ተጠቂዎችን ያማካለ መሆን ነበረበት። ለእነርሱ ካሳ በሚሰጥ ብሎም ለቀሪው ሕብረተሰብ መቀጣጫ መሆን ነበረበት" ብለዋል።
"በተጨማሪም በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው በርካታ የኤርትራ ወታደሮች በጥቃቱ ተሳታፊ ነበሩ። በእነርሱ ላይ የተወሰደ የፍርድ ሂደት አለ ወይ የሚለውም ግልጽ አይደለም፤ ለዚያ ነው በቂ አይደለም የምንለው" ሲሉ ፍስሃ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አምነስቲ ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚያካሂዳቸው ምርመራዎች የፖለቲካ ወገንተኝነት ይጫነዋል የሚሉ ክሶችን ውድቅ ያደረጉት ፍስሃ "የሰብአዊ መብት ጥናት ሲሰራ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ ይከናወናል። ትግራይ ውስጥ ያለው ግጭት ያስከተላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መጠነ ሰፊ ናቸው። ነገር ግን መገናኛ ብዙኃን ላይ ስለወጡ ብቻ ሪፖርት እናወጣለን ማለት አይደለም" ሲሉ ፍስሃ ገልጸዋል።












