በትግራይ በሦስት ወራት ውስጥ ከ1ሺህ በላይ የሚሆኑ ሴቶች መደፈራቸውን ሪፖርት ማድረጋቸውን አምነስቲ ገለጸ

በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭቱ ሲቀሰቀስ በትግራይ የነበረች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭቱ ሲቀሰቀስ በትግራይ የነበረች ሴት

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ለወራት በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ የተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችን የዳሰሰበትን የጥናት ውጤት ይፋ አደረገ።

አምነስቲ ከተለያዩ የጤና ተቋማት በሰበሰበው መረጃ መሠረት ከየካቲት እስከ ሚያዚያ ባሉት ወራት ብቻ በጦርነቱ አውድ ውስጥ 1288 የሚሆኑ የመድፈር ጥቃቶች የተፈጸመባቸው ተጠቂዎች ወደ ህክምና መስጫ ተቋማት ሄደው ሪፖርት ማድረጋቸውን አመላክቷል።

ለጥናቱ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው 68 የጥቃቱ ሰለባዎች መካከል አብዛኛዎቹ ወደ ጤና ተቋም አለመሄዳቸውን በመጥቀስ ወደ ሕክምና ተቋማት የሄዱ ሰዎች ቁጥር የጥቃቱን ስፋት አያሳይም ሲል አምነስቲ ጠቅሷል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት እና ተቋማት ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በትግራይ እየተፈጸሙ ነው ሲሉ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን ማቋቋሙን እና በወንጀሉ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ ስለመኖራቸው ሲገልጽ ነበር።

የሪፖርቱን ውጤት ተከትሎ ቢቢሲ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽህፈት ቤት እና የአማራ ክልል የሕዝብ ግንኙነት አስተያየትን ለማካተት ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

በቡድን የተፈጸሙ መድፈር ጥቃቶች

አምነስቲ ካነጋገራቸው 68 የጥቃቱ ሰለባዎች ውስጥ ብዙሃኑ ከአንድ በላይ በሆኑ ሰዎች ተደፍረዋል። ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ነፍሰጡርና ኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሲሆኑ የተወሰኑት በልጆቻቸው ፊት የተደፈሩ መሆናቸውን ሪፖርቱ በዝርዝር አስነብቧል።

አምነስቲ ካነጋገራቸው 68 ሰዎች መካከል 38ቱ በቡድን የተደፈሩ ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል የባአከር ከተማ ነዋሪ የነበረች የ20 ዓመት ወጣት ሴት ትገኝበታለች።

"ኅዳር 28 ወደ ቤታችን የጦር መሳሪያ እንፈትሻለን ብለው ሁለት የደንብ ልብስ የለበሱ እና አንድ ሲቪል ልብስ የለበሰ ታጣቂዎች መጡ። አባቴም መተኛቴን ሲነግራቸው ሳይረብሹኝ ፈትሸው እንደሚወጡ ነግረውት ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎችን አስወጥተው ወደኔ መጡ። ሲነጋገሩ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ከዚያም ድምጽ እንዳላሰማ በምልክት አስጠንቅቀውኝ በየተራ ደፈሩኝ። የአራት ወር ነብሰ ጡር መሆኔን ይረዱ አይረዱ አላውቅም። ሰው መሆኔንም ይረዱ አይረዱ አላውቅም" ስትል የገጠማትን ለአምነስቲ አስረድታለች።

በሪፖርቱ ለደኅንነቷ ሲባል ንግሥት የሚል ስም የተሰጣት የ25 ዓመት እናትም በሽራሮ ከተማ እርሷ እና ሌሎች አራት ሴቶች በኤርትራዊያን ወታደሮች መደፈራቸውን ተናግራለች።

ከሁመራ በመሸሽ ላይ የነበሩት ንግሥት እና አብረዋት የነበሩት ሴቶች በቡድን መደፈራቸውንም ትናገራለች።

"ከመሃላችን አንደኛዋ የስምንት ወር እርጉዝ ነበረች፤ ለአምስት ደፈሯት። በዚህ ምክንያት ልጇን ያለጊዜው ወለደች" ትላለች።

ንግስሥ የሁለት ዓመት ልጇ እየተመለከተ እርሷም በቡድን መደፈሯን ትናገራለች። "ለሦስት ከደፈሩኝ በኋላ አራተኛው ሊደፍረኝ ሲመጣ ከመሃል አንደኛው ተዋት ብሎ አስጣለኝ" ስትል የሰጠችው ቃል በሪፖርቱ ላይ ተካቷል።

የባድመ ከተማ ነዋሪ የነበረችው የምስራች ኤችአይቪ በደሟ ውስጥ እንደሚገኝ ብትገልጽላቸውም አራት የኤርትራ ወታደሮች እንደደፈሯት ሪፖርቱ አስነብቧል።

በስልካቸው የወሲብ ቪዲዮ ሲመለከቱ እንደነበር ብሎም በቪዲዮ ላይ ያሉ ተግባራትን እንድትፈጽም እንዳስገደዷት ተናግራለች።

የወሲብ ባርነት

አምነስቲ ካነጋገራቸው 68 ሴቶች ውስጥ 12ቱ ለቀናት እና ለሳምንታት በቆየ የወሲብ ባርነት ውስጥ እንደነበሩ ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ህጻናት ሲሆኑ አንዳንዶቹ በጦር ካምፖች፣ ሌሎቹ በመኖሪያ ቤቶች አንዲሁም በሜዳ ላይ ለቀናት ተይዘው መቆየታቸውን ተቋሙ ገልጿል።

የ21 ዓመቷ ብሌን በባድመ ከተማ የሆቴል አስተናጋጅ እንደነበረች ሪፖርቱ አስነብቧል። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ወታደሮች ታግታ መወሰዷን እና ከሌሎች 30 ከሚሆኑ ሴቶች ጋር ለ40 ቀናት በወሲብ ባርነት ውስጥ መቆየቷን ለአምነስቲ ተናግራለች።

"የደፈሩኝ አምስት ወይም ስድስት ይሆናሉ። ኤርትራ ውስጥ የሚገኝ ጋሽባርካ ወደሚባል አካባቢ ከወሰዱን በኋላ ነው የደፈሩን። ሁላችንም ተደፈርናል። ከ40 ቀናት በኋላ ወደ ባድመ አምጥተው ለቀቁን" ስትል ለአምነስቲ አስረድታለች።

የሁመራ ከተማ ነዋሪ የነበረችው ጸዳለ በሁመራ ከተማ በአማራ ልዩ ኃይል ታስራ በቆየችበት ወቅት በቀን ሶስቴ እንደምትደበደብ እና መደፈሯንም ገልጻለች። "ሦስት ወንዶች በየተራ በየምሽቱ ይደፍሩኝ ነበር" ስትል ለአምነስቲ ተናግራለች።

የታጣቂዎቹ ሁኔታ

በሪፖርቱ ላይ ተሳታፊ የሆኑት የአምነስቲ ከፍተኛ መርማሪ ዶናቴላ ሮቬራ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንዲሁም የአማራ ኃይሎች "አጥቂ" ተብለው በተጠቂዎች ተለይተዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች አጥቂዎቹን በሚናገሩት ቋንቋ እንዲሁም በደንብ ልብሳቸው እንደለዩ ዶናቴላ አክለዋል።

"በመካከለኛው ምሥራቅ ብሎም በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች ባሉ የግጭት አካባቢዎች ተዘዋውሬ የጾታ ጥቃቶችን መርምሬያለሁ። አሁን የሰማኋቸው ምስክርነቶች ግን እጅግ አስከፊው ናቸው" ሲሉ ዶናቴላ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቀጣይ እርምጃ

አምነስቲ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የተመድ የሕግ የበላይናት እና የጾታዊ ጥቃት ጉዳዮችን የሚመለከተው ቡድን ምርመራ አካሂደው ጥፋተኞች ለሕግ እንዲቀርቡ ጥሪውን አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በግጭቱ ወቅት ደረሱ የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን መቋቋሙን አስታውቆ ነበር።

ጾታዊ ጥቃት ፈጽመዋል የተባሉ የሠራዊት አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ጠቅላይ ሚንሰትሩ ከዚህ ቀደም ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የአምነስቲ የምሥራቅ አፍሪካ አጥኚ የሆኑት ፍስሃ ተክሌ በቁጥጥር ሥር ዋሉ የተባሉት ሰዎች ቁጥር ከደረሰው ጉዳት ስፋት ጋር የማይነጻጸር ነው ይላሉ።

አክለውም "የጾታዊ ጥቃቶች ፍርድ ሂደት ተጠቂዎችን ያማካለ መሆን ነበረበት። ለእነርሱ ካሳ በሚሰጥ ብሎም ለቀሪው ሕብረተሰብ መቀጣጫ መሆን ነበረበት" ብለዋል።

"በተጨማሪም በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው በርካታ የኤርትራ ወታደሮች በጥቃቱ ተሳታፊ ነበሩ። በእነርሱ ላይ የተወሰደ የፍርድ ሂደት አለ ወይ የሚለውም ግልጽ አይደለም፤ ለዚያ ነው በቂ አይደለም የምንለው" ሲሉ ፍስሃ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል የግንኙነት መስመሮች ተቋርጠው ስለሚገኙ እነዚህ ጥቃቶች ቀጥለዋል ወይም ቆመዋል የሚለውን ለማጣራት አለመቻላቸውንም ፍስሃ አክለዋል።

"እነዚህ ጥቃቶች ቀጥለው ከሆነ ወደፊት ግንኙነት ሲመለስ የምንከታተለው ይሆናል። የጾታዊ ጥቃቶች ብቻ ሳይሆን ሌሎች የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። አሁን ላይ እነዚህን ማረጋገጥ አልቻልንም" ሲሉም አክለዋል።

አምነስቲ ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚያካሂዳቸው ምርመራዎች የፖለቲካ ወገንተኝነት ይጫነዋል የሚሉ ክሶችን ውድቅ ያደረጉት ፍስሃ "የሰብአዊ መብት ጥናት ሲሰራ ከፍተኛ የሆነ የመረጃ ማሰባሰብ ስራ ይሰራል። ትግራይ ውስጥ ያለው ግጭት ያስከተላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መጠነ ሰፊ ናቸው። ነገር ግን መገናኛ ብዙሃን ላይ ስለወጡ ብቻ ሪፖርት እናወጣለን ማለት አይደለም" ሲሉ ፍስሃ ገልጸዋል።

ጦርነቱ ወደ አማራ እና ወደ አፋር ክልል መስፋፋቱን በተመለከተ የሰብአዊ መብት ጥቃቶችም ሊስፋፉ እንደሚችሉ አጥኚው አክለዋል።

ይህንንም ተከትሎ እየተሰሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ተቋማቸው ጊዜ ወስዶ እንደሚያጣራም ፍስሃ ለቢቢሲ ተናግረዋል።