ህወሓት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለመተባበር መስማማታቸውን አረጋገጡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኢትዮጵያ መንግሥት ኦነግ-ሸኔ የሚለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን ከህወሓት ጋር ወታደራዊ ትብብር ለማደረግ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን የቡድኖቹ መሪዎች አረጋገጡ።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪ ኩምሳ ድሪባ ለአሶሺየትድ ፕሬስ የህወሓት መሪ የሆኑት ደብረ ጺዮን ገብረ ሚካኤል ደግሞ ለሮይተርስ ዜና ወኪሎች እንደተናገሩት ቡድኖቻቸው የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመጣል ትብብር ለመፍጠር ንግግር ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል።
ቀደም ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ሁለቱ ቡድኖች በመተባበር የአገሪቱን ሠላምና አንድነት ለማናጋት እየሰሩ ነው ሲል በተደጋጋሚ ሲከስ የቆየ ሲሆን ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ የአገሪቱ ምክር ቤት ቡድኖቹን አሸባሪ ድርጅቶች በማለት መሰየሙ ይታወሳል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በምዕራብ እና በደቡብ የኦሮሚያ ክፍሎች እንደሚንቀሳቀስ የሚናገረው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በተለይ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ሲነሳ ቆይቷል።
ከጥቅምት ወር ጀምሮ ከመንግሥት ጋር ከባድ ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ የገባው ህወሓት ከሳምንታት በፊት ከትግራይ ክልል ባሻገር ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የትግራይ ክልሎች በመግባት ጥቃት እየሰነዘረ ይገኛል።
"አሁን ያለው ብቸኛ መፍትሄ መነጋገር በሚፈልጉት ቋንቋ በማናገር በወታደራዊ ኃይል ከሥልጣን ማስወገድ ነው" ሲል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መሪ የሆነው መሮ በመባል የሚታወቀው ኩምሳ ድሪባ ለኤፒ ተናግሯል።
ኩምሳ ድሪባ እንዳለው ቡድኑ ከህወሓት ጋር ከስምምነት የደረሰው ከጥቂት ሳምንታት በፊት የትግራይ ኃይሎች ባቀረቡት ሐሳብ መሰረትነት ነው።
"በጋራ ጠላታችን ላይ በተለይ ወታደራዊ ትብብር ለማድረግ በመግባባት ደረጃ ከስምምነት ላይ ደርሰናል" በማለት የውጊያ መረጃዎችን መለዋወጥና ጎን ለጎን ሆነው እየተዋጉ ባይሆንም ሁኔታዎች በሚፈጠሩ ጊዜ ለመተባበር ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን አመልክቷል።
ከሮይተርስ ዜና ወኪል ጋር በሳተላይ ስልክ የተናጋገሩት ዶ/ር ደብረ ጺዮን ከቡድኑ ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን ቢያረጋግጡም ተጨማሪ ዝርዝር ከመናገር ተቆጥበዋል።
የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት ጌታቸው ረዳም እንዲሁ "አንዳች አይነት ስምምነት" ላይ ለመድረስ ሥራዎች እየተሰሩ ነበር ሲል ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ጨምረውም "በኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ላይ ድርሻ ካላቸው ወገኖች ጋር በጋራ መሥራት ምንም አዲስ ነገር የለውም" ሲሉ ተናግረዋል።
ኩምሳ ድሪባ በበኩሉ ለአሶሺየትድ ፕሬስ እንደተናገረው ፖለቲካዊ ትብብር ለመፍጠር ንግግር እየተደረገ መሆኑን በማመልከት ሌሎች ቡድኖችም በተመሳሳይ ውይይቶች ውስጥ እየተሳተፉ በመሆናቸው "ይህም ያለውን መንግሥት የሚቃወም ትልቅ ትብብር ይሆናል" ሲል ለአሾሺየትድ ፕሬስ ተናግሯል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ቢለኔ ስዩም ሁለቱን ቡድኖች በተመለከተ በኢሜል በሰጡት ምላሽ ህወሓት እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በአገሪቱ ፓርላማ ሽብርተኛ ድርጅቶች መሆናቸውን ከመጥቀስ ውጪ ዝርዝር እንዳልሰጡት ለሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።
ህወሓት ከሦስት ዓመት በፊት የተካሄደውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በኢህአዴግ ውስጥ በተካሄደ የለውጥ ሂደት ከማዕከላዊው መንግሥት ውስጥ የነበረውን ቁልፍ ሚና በማጣት መቀመጫውን ትግራይ አድርጎ ቆይቶ ከፌደራሉ መንግሥት ጋር ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ገብቷል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ለረጅም ዓመታት መቀመጫውን በኤርትራ አድርጎ የትጥቅ ትግል ሲያደርግ የቆየውና ከለውጡ በኋላ በሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ ለመንቀሳቀስ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰው ኦነግ የተገነጠለ ታጣቂ ቡድን ነው።














