ሊቢያ ውስጥ ተቀጥሮ የነበረው የሩሲያ "ነብሰ ገዳይ ኩባንያ" ማን እንደነበረ ተደረሰበት

የዋግነር ተዋጊ በሊቢያ
የምስሉ መግለጫ, የዋግነር ተዋጊ በሊቢያ

የሙአሙር ጋዳፊን ግድያ ተከትሎ በጦርነት ትታመስ በነበረችው የሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ሊቢያ ለዓመታት በጦርነት ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርግ የነበረው የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊ ኩባንያ ማንነትና ተግባራት ተጋለጡ።

ቢቢሲ ጊዜ ወስዶ በሠራው ሰፊ የጋዜጠኝነት ምርመራ እንደደረሰበት ከሆነ ይህ ድርጅት ዋግነር የሚባልና ባለቤትነቱም ከአንድ ሩሲያዊ ባለሀብት ጋር ሊገናኝ እንደሚችል ፍንጭ ተገኝቷል።

የቢቢሲ የምርመራ ውጤት ዋግነር ቅጥረኛ የጦር ተዋጊዎች ኩባንያ በሊቢያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተሳትፎው እስከምን ድረስ እንደነበር ያጋለጠ ነው።

ለዚህ ምርመራ መነሻ የሆነው ተጥሎ የተገኘና ከሊቢያ ደኅንነት ሰዎች ለቢቢሲ የደረሰ አንድ የሳምሰንግ ታብሌት ነው።

ይህ ታብሌት በአንድ ሽሽት ላይ በነበረ የዋግነር ኃይል ቡድን አባል ተጥሎ የተገኘ ሲሆን በውስጡ ቁልፍ መረጃቸውን እንደያዘ ተደርሶበታል።

ለምሳሌ በሊቢያ ይገኙ የነበሩ ሩሲያዊ ነፍሰ ገዳዮች፣ የጦር አበጋዞች ምስጢራዊ ስም፣ የመሣሪያ ግዥ ዝርዝርና ሌሎችም ጠቃሚ የጦር መረጃዎችን የያዘ ነው።

ከሊቢያ ደኅንነት ሰዎች ለቢቢሲ የተሰጠ የሳምሰንግ ታብሌት
የምስሉ መግለጫ, ከሊቢያ ደኅንነት ሰዎች ለቢቢሲ የተሰጠ የሳምሰንግ ታብሌት

በዚህ ታብሌት ውስጥ የተዘረዘሩ የጦር መሣሪያ ዓይነቶች ከሌላ ከየትኛውም አገር የማይገዙና የሩሲያ ምርት የሆኑ እንደሆኑም በምርመራው በማያዳግም ሁኔታ ተጋልጧል።

ሩሲያ ከዋግነር የቅጥር ተዋጊዎች ጦር ኩባንያ ጋር ግንኙነት የለኝም ስትል አስተባብላለች።

ይህ የጦር ተዋጊዎች ኩባንያ በፈረንጆቹ 2014 ነበር ለመጀመርያ ጊዜ ማንነቱ የተሰማው።

ያን ጊዜ ከዩክሬን መገንጠል እንፈልጋለን የሚሉ የሩሲያ ደጋፊ ተገንጣዮችን በማገዝ ለውጊያ የጦር ድጋፍ ሲሰጥ የነበረ ኩባንያ ነው።

ከዚያ በኋላ ይህ የጦር ተዋጊዎች ኩባንያ ስሙ በሩሲያ፣ ሞዛምቢክ፣ ሱዳን እና ሴንትራል አፍሪካን ሪፐብሊክ ተደጋግሞ ሲነሳ ነበር።

የዋግነር ቅጥር ተዋጊዎች ቡድን በሊቢያ ለመጀመርያ ጊዜ የታየው እአአ 2019 ሲሆን ያን ጊዜ የቡድኑ መቺ ኃይል ወደ ሊቢያ ምድር የገባው የጦር አበጋዙን ጄኔራል ኻሊፋ ሐፍጣርን ለማገዝ ነበር።

ያን ጊዜ ሐፍጣር በተባበሩት መንግሥታት ይደገፍ የነበረውን የትሪፖሊውን መንግሥት ለመፈንገል ጥቃት የከፈተበት ጊዜ ነበር።

ይህ ዋግነር የተዋጊዎች ቡድን እጅግ ምስጢራዊ እንደሆነ ይነገራል።

ሆኖም ቢቢሲ ለዚህ ኩባንያ በተዋጊነት ከተሰለፉ የቀድሞ ሁለት ጦረኞች ጋር ግንኙነት በማድረግ መረጃዎችን ሰብስቧል።

ሁለቱ ግለሰቦች ዋግነር ምን ዓይነት ሰዎችን እንደሚቀጥርና የጦርነት ሥነ ምግባርን በጭራሽ እንደማይከተል እንዲሁም በጭካኔው ወደር እንደሌለው አጋልጠዋል።

ዋግነር ቅጥር የጦር ተዋጊዎች ለምሳሌ እስረኛ ወይም ምርኮኛን መመገብ አላስፈላጊ ወጪ ነው ብለው ስለሚያስቡ መግደልን ይመርጣሉ ሲሉ የቀድሞ ሁለት አባላቱ መስክረዋል።

'ማንም የእስረኛን ሆድ በየቀኑ የመሙላት ፍላጎት የለውም' ሲል ከሁለቱ አንዱ ምስክርነቱን ለቢቢሲ ሰጥቷል።

ይህ ምስክርነት ከዚህ ቀደም ቢቢሲ አረብኛ ያስተላለፈው ሌላ ዘጋቢ ፊልም ይዘት ጋር የሚጣጣም ነው። በሊቢያ ሆን ብሎ ንጹሐንን መግደል እንደ አንድ የጦር ስትራቴጂ ተደርጎ ሲወሰድ ቆይቷል።

በዚህ ዘጋቢ ፊልም ላይ በምስክርነት የቀረበ አንድ ሊቢያዊ በጦርነት ውስጥ ዘመድ አዝማዶቹ ሲገደሉ እሱም የሞተ መስሎ በመጋደም አጮልቆ ያየውን አሰቃቂ ድርጊት አጋልጦ ነበር።

ይህን ግድያ በልጁ ቤተሰብ የፈጸመውን ግለሰብም ቢቢሲ መለየት ችሏል።

አንድ ሊቢያዊ በጦርነት ወቅት የተገደለ የዘመዱን ፎቶግራፍ አሳይቷል።
የምስሉ መግለጫ, አንድ ሊቢያዊ በጦርነት ወቅት የተገደለ የዘመዱን ፎቶግራፍ አሳይቷል።

ሌላ የዓይን እማኝ አንድ የሊቢያ መንግሥት ወታደር እንዴት ለዋግነር ቅጥር ተዋጊዎች እጁን ከሰጠ በኋላ ሆን ተብሎ ሆዱ ላይ ሁለት ጊዜ በመተኮስ እንዲገደል እንደተደረገ መስክሯል።

ቢቢሲ እጅ የገባው የሳምሰንግ ታብሌት ቅጥር የሩሲያ ተዋጊዎች እንዴት ሰላማዊ ሰዎች በሚኖሩበት ቦታ ፈንጂ እንደሚቀብሩም ፍንጭ ይሰጣል።

በጦርነት ሕግ ፈንጂዎችን ምልክት ሳያደርጉ በሰላማዊ ቦታዎች መቅበር የጦር ወንጀል ሆኖ ያስከስሳል።

ይህ ሳምሰንግ ታብሌት በደቡብ ትሪፖሊ አካባቢ በእአአ 2020 በጸደይ ወቅት ከአንድ በመሸሽ ላይ የነበረ ቅጥር የሩሲያ ተዋጊ ጥሎት እንደሄደ ይገመታል።

በውስጡ ከያዛቸው መረጃዎች መካከል የውጊያ ካርታዎች፣ ቅጥር ተዋጊ ሩሲያዊያን የሚይዟቸውና የሚዋጉባቸው ግንባሮች ይገኙበታል።

ከዚህም ባሻገር እንዲገዙ የታሰቡ ውስብስብ የጦር መሣሪያዎች ዝርዝርና ዋጋ የያዘ ሲሆን እነዚህ የጦር መሣሪያዎችም ሙሉ በሙሉ ሩሲያ ሰራሽ ናቸው።

10 ገጽ በያዘው በዚህ ዝርዝር ውስጥ አራት ታንኮች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክላሺንኮፍ ጠመንጃዎች እና የራዳር ሲስተሞች በግዢ እንዲመጡ ይዘረዝራል።

በዋግነር የቅጥር የሩሲያ ተዋጊ ቡድን ጥናት ያደረጉ አንድ ተንታኝ የግዢ ዝርዝሩ ሲታይ የሩሲያው ዲሚትሪ ዩትኪን እጃቸው እንዳለበት የሚያመላክት ነው።

ዲሚትሪ የቀድሞ የሩሲያ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቁልፍ ሰው ሲሆኑ ዋግነር የቅጥረኛ ተዋጊዎች ኩባንያን እንደመሰረቱ ይገመታል። ቢቢሲ ዲሜትሪ ዩትኪንን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

በታብሌቱ ውስጥ ከተገኙ ሌሎች መረጃዎች በመነሳትም የቭጌኔ ፕሪጎዚን ስም ተመላክቷል። እኚህ ሩሲያዊ ቢሊየነር የቪላድሚር ፑቲን ምስጢረኛና ወዳጅ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በጉዳዩ ላይ ከቢቢሲ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ የሩሲያ መንግሥት በሊቢያ ሰላም እንደሚጣ እየሠራ ነው የሚል ነው።

በታብሌት ውስጥ የተገኘው መረጃም ሐሰት ነው ሲል አስተባብሏል።

ዋግነር የሩሲያ ቅጥር ተዋጊዎች ቡድን ሩሲያ በሌሎች አገሮች ላይ ለሚኖራት ፖለቲካዊ ፍላጎት ወታደራዊ ምላሽ የሚሰጥ ድርጅት እንደሆነ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ የቀድሞ የኩባንያው አባል ለቢቢሲ ተናግሯል።

አባላት የሚደረጉት ደግሞ ሥራ አጦች፣ የጦር አዋቂዎችና በሩሲያ ብሔራዊ ስሜት ተነሳስተው በተዋጊነት ለማገልገል ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦች ናቸው።