በቶኪዮ ኦሊምፒክስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ የመጀመሪያዎቹ ስፖርተኞች ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቶኪዮ ኦሊምፒክስ ከመጀመሩ ከአምስት ቀናት በፊት በአትሌቶች መንደር ውስጥ ሁለት ስፖርተኞቸ ኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው የመጀመሪያዎቹ ተወዳዳሪዎች ሆነዋል፡፡
አዘጋጆቹ እንደሚሉት ሁለቱ ስፖርተኞች ቅዳሜ ዕለት ተመርምረው ቫይረሱ ከተገኘባቸው ባለሥልጣን ጋር በተመሳሳይ ቡድን እና ስፖርት ዘርፍ የሚገኙ ናቸው ተብሏል፡፡
ሌሎች የቡድኑ አባላት በክፍላቸው ተለይተው እንዲቀመጡ ተደርጓል።
በመንደሩ ቫይረሱ የተገኘባቸው የመጀመሪያዎቹ ስፖርተኞቹ ሲሆኑ ሌላ ቦታ አንድ ተጨማሪ ስፖርተኛ እሑድ ዕለት በተመሳሳይ ቫይረሱ ተገኝቶበታል፡፡
አዘጋጆቹ በአጠቃላይ እሁድ ዕለት ጋዜጠኞች፣ ተባባሪ አካላትን እና ሌሎች ሠራተኞችን ጨምሮ ከኦሎምፒክ ጋር የተገናኙ 10 አዳዲስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ሪፖርት ተድርገዋል፡፡
ቅዳሜ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 15 ነበር፡፡
በቶኪዮ የቫይረሱ ስርጭት መጠን እየጨመረ ሲሆን ለአራት ተከታታይ ቀናት ከ 1ሺህ በላይ አዳዲስ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ተመዝግበዋል፡፡ ብዙ ጃፓናዊያን ውድድሩን መካሄዱን እንደሚቃወሙ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡
የቶኪዮ ኦሎምፒክስ ቃል አቀባይ ማሳ ታካያ እንደተናገሩት ሦስቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው "ከአንድ ሀገር እና ውድድር ዘርፍ የተገኙ ናቸው፡፡ ለጊዜው በክፍላቸው ተለይተው የሚቆዩ ሲሆን ምግብ እየተሰጣቸው ነው።" ቀሪዎቹ የቡድኑ አባላትም ተመርምረዋል ብለዋል።
የውድድሩ ኃላፊ ሴኮ ሃሺሞቶ ቅዳሜ ዕለት "ወደ ጃፓን የሚመጡ ስፖርተኞች ምናልባት በጣም ተጨንቀው ሊሆን እንደሚችል ተረድቻለሁ" ብለዋል፡፡
"ማንኛውንም የኮቪድ ወረርሽኝ ለመከላከል ሁሉንም ነገር እያደረግን ነው፡፡ ወረርሽኝ ካጋጠመንም ምላሽ ለመስጠት ዕቅድ መያዙን እናረጋግጣለን፡፡"
የቶኪዮ ኦሎምፒክ የአውስትራሊያ ቡድን የኮቪድ-19 ስጋት በመኖሩ ካይረን በሚገኘው የቅድመ ውድድር ማሠልጠኛ ማዕከል ራሳቸው ለይተው በየክፍላቸው ተቀምጠዋል፡፡
እሁድ የአውስትራሊያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ምርመራዎች አባላቱ ቫይረሱ እንደሌለባቸው አረጋግጧል ብሏል።
አትሌቶች ከምርመራው በኋላ በዝግጅት ውድድር እንዲሳተፉ ተፈቅዶላቸዋል።
የአውስትራሊያ ኦሎምፒክ ዋና የሕክምና መኮንን የሆኑት ዴቪድ ሂዩዝ "በእኔ ግንዛቤ [የአውስትራሊያ አትሌቲክስ] የተትረፈረፈ ጥንቃቄን ተግባራዊ አድርጓል" ብለዋል፡፡












