የአፍጋኒስታን አምባሳደር ልጅ ፓኪስታን ውስጥ ታግታ እንደነበር ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Najib Alikhil on Twitter
በፓኪስታን የአፍጋኒስታን አምባሳደር ሴት ልጅ ባልታወቁ ሰዎች ለሰዓታት ታግታ ጉዳት ደርሶባታል ሲሉ ባለስልጣናት ገለጹ፡፡
ሲልሲላ አሊሂል አርብ ዕለት በፓኪስታን ዋና ከተማ ኢስላማባድ ወደ ቤቷ በምትሄድበት ወቅት ታግታ ለተወሰኑ ሰዓታት ቆይታለች፡፡
የአፍጋኒስታን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩሉ "ከፍተኛ ስቃይ ደርሶባታል" በማለት ቅሬታ እያቀረበ ነው፡፡
በሁለቱ ጎረቤት ሃገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ለረዥም ጊዜ የተበላሸ ሆኖ ቆይቷል፡፡
የፓኪስታን ባለሥልጣናት እንደሚሉት በ 20ዎቹ ዕድሜ ላይ የምትገኘው ሲልሲላ አሊሂል ከምትጓዝበት መኪና ውስጥ ታፍና ተወስዳ በጥቃት አድራሾቹ ጥቃት ደርሶባታል፡፡
ከተለቀቀች በኋላ በሆስፒታል ህክምና እንዳገኘች የተገለፀ ሲሆን አምባሳደሩ ናጂብ አሊሂል "ኢ-ሰብአዊ ጥቃቱን" በማውገዝ ሴት ልጃቸው "አሁን ጥሩ ስሜት ይሰማታል" ብለዋል፡፡
የአፍጋኒስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር "ስጋቱን" በመግለፅ ፓኪስታን ለዲፕሎማቶች እና ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ዋስትና እንድትሰጥ አሳስበዋል፡፡
የፓኪስታን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአምባሳደሩ ጥበቃ መጠናከሩን አስታውቋል፡፡
የፓኪስታን የሀገር ውስጥ ሚኒስትር ሼክ ራሺድ አህመድ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካሃን ወንጀለኞቹ በፍጥነት በቁጥጥር ስር እንዲውሉ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአፍጋኒስታን እየጨመረ በሚመጣው አመጽ ምክንያት የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት እየተቀዛቀዘ መጥቷል፡፡
የአፍጋኒስታን መንግሥት በመላ ሀገሪቱ አመጽ ለሚያካሂዱ የታሊባን ታጣቂዎች መጠለያ በመስጠት ፓኪስታንን ይከሳል፡፡
የታሊባን ታጣቂዎች ከአፍጋን ኃይሎች የድንበር አካባቢዎችን በመያዝ ግስጋሴዎቹን አጠናክሯል፡፡
ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከሰጡት ከመስከረም 11 የጊዜ ገደብ በፊት አሜሪካ ኃይሎቿን ከሃገሪቱ የማስወጣቷን እንቅስቃሴዋን ስታጠናቅቅ ታሊባን በፍጥነት ተንቀሳቅሷል፡፡
እንግሊዝን ጨምሮ ሌሎች አጋር ሃገራት ከባይደን የጊዜ ገደብ በፊት ሁሉንም ወታደራዊ ኃይሎቻቸውን አስወጥተዋል፡፡
ፓኪስታን በበኩሏ የአፍጋኒስታን ታጣቂዎች ከድንበሯ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ፈቅዳለች በሚል ትከሳለች፡፡












