የውጭ ሚዲያዎች ከትግራይ ጋር በተያያዘ በሚጠቀሙት አገላለጾች ዙሪያ ማሳሰቢያ ተሰጠ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Media Authority
የውጭ አገር ሚዲያዎች የትግራይን ጦርነት በሚዘግቡበት ወቅት 'የትግራይ መከላከያ ኃይል' ከማለት እንዲቆጠቡ የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን አሳስቧል።
ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ዘገባዎችን ገምግሞም ህወሓትን ብሔራዊ ሠራዊት እንዳለው የትግራይ መከላከያ ኃይል እያሉ የሚጠሩ አንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች አሉ ብሏል።
በመግለጫውም ላይ እንደተጠቀሰው የትግራይ ክልል ከኢትዮጵያ ፌዴሬሽን አንዷ አካል ናት ካለ በኋላም የመከላከያ ኃይል ሊኖራትም አይችልም ብሏል።
ህወሓት ከፌደራል መንግሥት ጋር ጦርነት ከገባ በኋላ የተለያዩ ኃይሎችንና ከማኅበረሰቡ የተውጣጣ ኃይል መስርቻለሁ በማለት የትግራይ መከላከያ ኃይል በሚልም እየተጠራ ይገኛል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ ሚዲያዎችም ኃይሉ ራሱን በሚጠራበት የትግራይ መከላከያ ኃይል እያሉም እየጠሩት ይገኛሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ህወሓትን ሽብርተኛ ብሎ ከመሰየሙ ጋርም ተያይዞ እንዲህ አይነት ስያሜዎችን መጠቀም የአገሪቱን የግዛት አንድነት፣ ብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነት የሚጥስ ነው ብሏል።
የተወካዮች ምክር ቤት በኅዳር ወር በሕገ መንግሥታዊ መሰረት የትግራይ ክልል መንግሥትን አፍርሶ ጊዜያዊ አስተዳደር መስርቷል ተብሏል።
በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ ሪፖርቶችም ላይ እንዲሁ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ተብሎ የሚጠቀስ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ቀኑን እስኪያስታውቅ ድረስ የትግራይ መንግሥት የለም ብሏል።
እስከዚያውም ድረስ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እየመራ ይቆያል ብሏል መግለጫው።
የመገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን እንዲህ አይነት ቃላቶችን ከመጠቀም እንዲቆጠቡ ያሳሰበ ሲሆን እነዚህን ቃላቶች መጠቀም ማለት የኢትዮጵያን ሕግ የሚጥስና ጥብቅ እርምጃም የሚወስድ መሆኑን አሳስቧል።
ይህ ማሳሰቢያ የወጣው በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚዘጋጀውን አዲስ ስታንዳርድን የድረ ገጽ ሚዲያ ፍቃድ በጊዜያዊነት ማገዱን የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ካሳወቀ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
ባለሥልጣኑ ስለወሰደው እርምጃ በሰጠው ማብራሪያ አዲስ ስታንዳርድ በሽብርተኝነት የተፈረጀው ቡድን አጀንዳ ያራምዳል ሲል ወንጅሎታል።
"ይህም በተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ቡድን 'የመከላከያ ኃይል' ብሎ እስከመጥራት የደረሰ ነው" ሲል ገልጿል።
"ይህንን ጨምሮ ሌሎች ጥፋቶች ላይ ጥልቅ ምርመራ ይደረግበታል፤ እናም ተጨማሪ እርምጃዎች ይወሰዳሉ" ሲልም ባለሥልጣኑ አመልክቷል።
የአዲስ ስታንዳርድ መስራች ጸዳለ ለማ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውስድ ማሰባቸውን ገልጸዋል። "ምክንያቱም ይህ ትክክልለኛ ውሳኔ ነው ብለን ስለማናምን ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የክልሉ አርሶ አደሮች የግብርና ወቅት እንዳያልፋቸው በማለት የጠየቀውን የተኩስ አቁም የፌደራል መንግሥቱ መቀበሉን ማስታወቁ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን ለቆ የወጣ ሲሆን በወቅቱም ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የመንግሥት ባለስልጣን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገሩት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ ለቆ እንደወጣና የህወሓት ኃይሎች ሁሉንም መውጫዎች እንደተቆጣጠሩት ተናግረው ነበር።
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራር አባላት በአዲስ አበባ ይገኛሉ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞውን የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ፓርቲ ህወሓትን ከጥቂት ወራት በፊት አሸባሪ ቡድን ብሎ መሰየሙ ይታወሳል።












