በምዕራብ አውሮፓ በተከሰተ ጎርፍ ቢያንስ 120 ሰዎች መሞታቸው ተገለፀ

Local government handout image of Erftstadt-Blessem, where houses have collapsed and some residents are believed to be trapped (16 July)

የፎቶው ባለመብት, EPA

በምዕራብ አውሮፓ በተከሰተ አደገኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢያንስ 120 ሰዎች ሞተዋል።

በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ያሉበት አልታወቀም ተብሏል።

የጎርፍ መጥለቅለቁ በአስርት አመታት ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነም ተገልጿል።

ለጎርፍ መጥለቅለቁ መነሻ የሆነውም ከፍተኛ ዝናብ ወንዞችን እንዲሞሉ በማድረግ ዳርቻዎችን ሰብሮ መጥለቅለቅን ፈጥሯል ተብሏል።

ምዕራብ አውሮፓንም እየጎዳት እንደሆነም ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት የሟቾች ቁጥር ከ100 በላይ በሆነባት ጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ቆፍጠን ያለ ትግል እንዲካሄድ ጥሪ አቅርበዋል።

በቤልጂየም 22 ሰዎች እንደሞቱ የአገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል። ኔዘርላንድስ፣ ሉክሰምበርግ እና ስዊዘርላንድም እንዲሁ ተጎድተዋል።

በጀርመን የሪይንላንድ-ፓላቲናቴ እና የሰሜን ራይን-ዌስትፋሊያ ግዛቶች በጎርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዱት መካከል ናቸው ተብሏል።

ሳይንቲስቶች በሰው ሰራሽ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ይህንን የመሰለ ከባድ የዝናብ መጠን እንደሚያመጣ በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ነበር።

በምዕራብ ጀርመን አውራዌይል አውራጃ ውስጥ እስከ 1 ሺህ 300 የሚደርሱ ሰዎች ያሉበት እንደማይታወቅ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

የአከባቢው መንግስት ቃለ አቀባይ በበኩላቸው የሞባይል ኔትወርኮች ከስራ ውጭ ስለሆኑ ብዙ ሰዎችን ማግነት እንዳልተቻለም ተናግረዋል።

700 ነዋሪዎች ያሉባት የሹልድ መንደር ሙሉ በሙሉ ወድሟል።

በኮሎኝ አቅራቢያ በምትገኘው ኤርፋስታት-ብረምም ከተማ ውስጥ የጎርፍ መጥለቅለቁ የተከታታይ ቤቶች እንዲፈርሱ ምክንያት ሆኗል።

የአካባቢው ባለስልጣናት እንዳሉት በጎርፉ የተጠቁ ሰዎች አስቸኳይ ጥሪዎችን ቢያደርጉም በብዙ አካካቢዎች መደረስ አልተቻለም ተብሏል።

በቤልጂየም ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ራልታልስፔሬ አንድ ትልቅ ግድብ በትንሹ ሞልቶ ቢፈስም ግድቡ እንዳልተሰበረ ባለስልጣናቱ ገልፀዋል።