በሻገቱ የእርግዝና መከላከያዎች ምክንያት ኬንያ ውግዘት እየገጠማት ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኬንያ መንግሥት የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎችን በማሰራጨቱ ከፍተኛ ትችት እየተሰነዘረበት ነው፡፡
ክንድ ላይ የሚቀበሩ ሁለት አነስተኛ ዘንጎችን የተቀበሉ ተጠቃሚዎች በላያቸው ላይ ሻጋታ እንዳዩ ዘግበዋል፡፡
በተፈለገው ጊዜ ሊወጡ ቢችሉም የወሊድ መቆጣጠሪያዎቹ ቢያንስ ለአምስት ዓመታት ያገለግላሉ፡፡ ፕሮጄስትሮን የተባለ ሆርሞን በመልቀቅ ሴቶች በየወሩ እንቁላል እንዳይለቁ የሚያደርግ መከላከያ ነው።
ሻጋታ ፈጥረዋል የተባሉትን የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ወደ ተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተሰራጨው በመንግሥታዊው የህክምና አቅርቦት ኤጀንሲ ኬምሳ በኩል ነው፡፡
የኬንያው ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ እንደዘገበው የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎቹ የመጡት በተባበሩት መንግስታት የህዝብ ቁጥር ፈንድ በኩል ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ነው፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በመንግሥት መካከል በተፈጠረ የግብር ክርክር ምክንያት ሞምባሳ ወደብ ላይ ተቀምጠው ነበር፡፡
መዘግየቱ በኬንያ የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ላይ እጥረትን አስከትሏል፡፡
ከሁለት ወር በፊትም በተመሳሳይ ኬምሳ በአሉታዊ የጎንዮሽ ጉዳቶቹ ምክንያት በይፋ አገልግሎት ላይ የማይውል የኤች.አይ.ቪ መድኃኒት በማሰራጨቱ ትችት ቀርቦበታል፡፡
ውሳኔው ላይ የተደረሰው በኤች.አይ.ቪ መድኃኒቶች እጥረት ምክንያት ነው፡፡












