በምዕራብ አውሮፓ በተከሰተው ጎርፍ ቢያንስ 180 ሰዎች ሞተዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሰሞኑን በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የከፋ ጉዳት በደረሰባቸው የጀርመን እና የቤልጅየም ነዋሪዎች ውሃው መጉደሉን ተከትሎ አካባቢያቸውን የማፅዳት ስራ ጀምረዋል።
የነፍስ አድን ሠራተኞች ተጎጂዎችን ማፈላለጉን በቀጠሉበት በአሁኑ ወቅት የጉዳቱ መጠን ግልጽ እየሆነ መጥቷል።
በጎርፉ መጥለቅለቅ ምክንያት ቢያንስ 180 ሰዎች ሞተዋል እንዲሁም ደብዛቸው ያልታወቀ በርካቶች መኖራቸውን ተከትሎ የሟቾች ቁጥር ከዚህ የበለጠ ሊጨምር ይችላል ተብሏል።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች በኦስትሪያ ክልል በሳልዝበርግ ውስጥ ሰዎችን በጎርፍ ከተጥለቀለቁ ጎዳናዎች አከባባቢ የሚኖሩ ቤቶች ውስጥ ነዋሪዎችን ማዳን መቻላቸውም ተነግሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በጀርመን ውስጥ ስጋቱ ወደ ደቡባዊ ባቫሪያ ክልል ውስጥ የጨመረ ሲሆን በስፍራውም ከባድ ዝናብ ጎዳናዎችንና ቤቶችን እያፈራረሰ እንደሆነም ተነግሯል።
በምዕራብ ጀርመን ባለሥልጣናት የስታይንባቻታል ግድብ አካባቢ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዲወጡ ቢደረግም የግድቡ መፍረስ አደጋው እንደቀጠለም ተናግረዋል።
የአውሮፓ መሪዎች የጎርፍ መጥለቅለቁ ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ ነው ያሉ ሲሆን በስዊዘርላንድ ፣ በሉክሰምበርግ እና በኔዘርላንድስም ላይ ጉዳት አድርሷል።
ሳይንቲስቶች በሰው ሰራሽ የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ይህንን የመሰለ ከባድ የዝናብ መጠን እንደሚያመጣ በተደጋጋሚ ሲያስጠነቅቁ ነበር።
ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የዓለም ሙቀት መጨመር ኃይለኛ ዝናብ እንዲዘንብ አድርጎታል ይላሉ።
የኢንዱስትሪው ዘመን ከጀመረበት ወቅት ጀምሮ አለም በ1.2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀቷ ጨምሯል ተብሏል።
አራት የእሳት አደጋ ሰራተኞችን ጨምሮ በጀርመን በደረሰው የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 156 ሰዎች መሞታቸው ታውቋል ።
በጀርመን የሪይንላንድ-ፓላቲናቴ እና የሰሜን ራይን-ዌስትፋሊያ ግዛቶች በጎርፉ በከፍተኛ ሁኔታ ከተጎዱት መካከል ናቸው ተብሏል።
በምዕራብ ጀርመን አውራዌይል አውራጃ ውስጥ እስከ 1 ሺህ 300 የሚደርሱ ሰዎች ያሉበት እንደማይታወቅ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።
የጎርፉ ከፍታ በነበረበት ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጠፍተዋል ተብለው የነበረ ቢሆንም በባለፉት ቀናት መገኘት እንደቻሉም ተገልጿል።












