የአውሮፓ ሕብረት ኃላፊ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የአውሮፓ ሕብረት የውጭ እና የደኅንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል አባል አገራት በትግራይ ቀውስ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ለመጣል እንዲያስቡ ጠየቁ።
ኃላፊው "በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ በእጃችን ያሉ አማራጮችን ከግምት ውስጥ ማስገባት ይጠይቃል የሚል እምነት አለኝ። እናም እኔ እስከገባኝ ድረስ የመገደብ እርምጃዎች አማራጭ ጠረጴዛው ላይ መቀመጥ አለበት" በማለት በብራስልስ በተካሄደው የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳዮች ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ለስምንት ወራት በዘለቀው ጦርነት ምክንያትና የእርዳታ አቀርቦት በተደጋጋሚ በመስተጓጎሉ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል።
ቦሬል እንዳሉት የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ መንግሥት ያወጀው የተኩስ አቁም ስምምነት መሬት ላይ እንዲተገብር እንደሚፈልግ ነው። ክልሉ በአንፃሩ ከሌላው ዓለም ጋር እየተቆራረጠ ነው ብለዋል።
ከሁለት ሳምንት በፊት የትግራይ ኃይሎች መቀለን ጨምሮ በርካታ የክልሉን ግዛቶች መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ኤሌክትሪክ እና ቴሌኮምዩኒኬሽንን ጨምሮ መሰረታዊ አገልግሎቶችን ዘግቷል በሚል እየተወቀሰ ነው።
በባለፈው ሳምንት ኃላፊው "የተኩስ አቁም ማለት የክልሉን መብራት መቁረጥ እና አስፈላጊ የሚባሉ መሰረተ ልማትን ማውደም አይደለም" ብለው ነበር።
ታማኝ የሆነ የተኩስ አቁም ማለት አስቸኳይ እርዳታ የሚፈልጉ ሚሊዮኖች ህፃናት፣ ሴቶችና ወንዶች እንዲደርሳቸው የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ነው ብለዋል።
ኃላፊው አክለውም ህይወትን ማዳን የሁሉም ኃይሎች ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያወጀችው የተናጠል የተኩስ አቁም 'ከበባ' ነው እንዲሁም መንግሥት ረሃብ እየፈጠረ ነው በማለት የአውሮፓ ኮሚሽን ከሰሞኑ ያወጣውን ማስጠንቀቂያ ኢትዮጵያ ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ ያወጀችው "ተኩስ አቁም ሳይሆን ከበባ ነው ረሃብም እንደ ጦር መሳሪያ እያገለገለ ነው" በማለት የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺክ ለሕብረቱ ፓርላማ በሰጡት ገለፃ ተችተዋል።
በብራስልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኮሚሽነሩን ንግግግር አሳዛኝ በማለት ከበባ ነው መባሉንም ውድቅ እንዳደረገው ለቀረበው ክስ በሰጠው ምላሽ ላይ አስፍሯል።
ኮሚሽነሩ "የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማፍረስ፤ መውጫዎችን በመዝጋት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመበት ነው ማለታቸው መሬት ላይ ያለውን እውነታ ችላ በማለት በመንግሥት ላይ መሰረተ ቢስ ክሶችን መሰንዘርን መርጠዋል" ብሏቸዋል።
የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ቀጥተኛ የበጀት እርዳታን ያገደ ሲሆን የእርዳታ ሠራተኞችንም የሚያደናቅፉ ባለስልጣናትንም ጥቁር መዝገብ ውስጥ አካትታለሁ በሚል ማስጠንቀቁን 'ኢዩ ኦብዘርቨር' ባወጣው ዘገባ ጠቅሷል።
ሕብረቱ ድንበር አቋርጠው ወደ ሱዳን ለገቡ ስደተኞችም 118 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ መደረጉንም ተገልጿል።
በትግራይ ክልል የተነሳው ጦርነት 2 ሚሊዮን ነዋሪውን ከክልሉ ሲያፈናቅል 400 ሺህ ደግሞ ለረሃብ ተጋልጠዋል።
በያዝነው ሳምንት ሰኞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለትግራይ ክልል የላካቸው ሰብዓዊ እርዳታ ጭነት መቀለ መግባታቸው ተገልጿል።
በሁለት ሳምንት ውስጥ ለመጀሪያ ጊዜ የደረሰው ይህ እርዳታ በ50 የጭነት መኪኖች የተጓጓዘ ነው።
በመቀለ የደረሰው እርዳታ 900 ሜትሪክ ቶን ምግብና አስፈላጊ ቁሳቁስ ቢሆንም በክልሉ ካለው ችግር አንፃር ይህ ቁጥር በእጥፍ ማደግ አለበት ተብሏል።
ከአራት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አስቸኳይ እርዳታ በሚፈልግባት ትግራይ 10 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብና 150 ሺህ ሊትር ነዳጅ በየሳምንቱ መድረስ አለበት በማለት ድርጅቱ አፅንኦት ሰጥቷል።
በትግራይ ያሉ ዋነኛ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን ሁለት ድልድዮችም ከጥቅም ውጭ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
መቀለ በትግራይ ኃይሎች ከተያዘች ጀምሮ መብራት የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት፣ ባንክና ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።
ህወሓት ማዕከላዊው መንግሥት እርዳታን እያገደ ነው በሚል የሚወቅስ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ መሰረተ ልማቶችን መልሼ እየገነባሁ ነው ብሏል።
ከዚህ ባሻገር በትግራይ ክልል ከግንቦት 22/2013 ዓ.ም ጀምሮ ምንም አይነት በረራዎች የተቋረጡ ቢሆንም መንግሥት ከሰሞኑ የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ለሚፈልጉ ሁሉ ልዩ ፈቃድ እንደሚሰጥና በረራዎችም ከሰኔ 28/2013 ዓ.ም እንደሚጀመሩ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በልዩ ሁኔታ የፈቀደውን የሰብዓዊ እርዳታ በረራ አለመከልከሉንና በአሁኑም ወቅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መንገደኞችን ወደ ትግራይ ክልል ለማጓጓዝ ሁለት በረራዎች እንዲፈቀዱለት መጠየቁን ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ ቢገልፅም ህወሓት በበኩሉ መቀለን በኃይል እንደተቆጣጠረ ተናግሯል።
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በኩል ኢትዮጵያ የተኩስ አቁሙን ለማወጅ የወሰነችበት ሁኔታም ከሰሞኑ ተገልጿል።
ከዚህም መካከል አብዛኛዎቹ የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች በመገደላቸውና በመታሰራቸው እንዲሁም የቀሩትን ጥቂት የህወሓት አመራሮች ለመያዝ ሲባል ጦርነቱን መቀጠል አስፈላጊ ባለመሆኑ ነው ተብሏል።
በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች የግብርና ወቅታቸውን እንዳይስተጓጎል፣ የረድዔት ድርጅቶች የበርካቶችን ህይወት እንዲያድኑ እድል ለመስጠት እንዲሁም የግጭቱ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የትግራይ ሕዝብ ሰላም የሚያስፈልገው በመሆኑ እና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ከጠቀሷቸው ምክንያቶች ናቸው።
ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።












