በኢንተርኔት አማካይነት ሳያውቁ 'ለሽያጭ' የቀረቡ ሕንዳውያን ሙስሊም ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, HANA KHAN
አውሮፕላን አብራሪዋ ሀና ካሀን ከጓደኛዋ አንድ መልዕክት ሲደርሳት በጣም ነበር የደነገጠችው።
'ሱሊ ዲልስ' የተባለ መተግበሪያ [አፕ] ላይ የሀናን ፎቶ ያየች ጓደኛዋ ነበረች መልዕክቱን የላከችላት።
መተግበሪያው በርካታ የሴቶች ፎቶ ለጥፎ "ለዛሬ ገበያ የተዘጋጁ" ከሚል ማስታወቂያ ጋር አቅርቧል። ስለ መተግበሪያው ሰምታ የማታውቀው ሀና የጓደኛዋ መልዕክት ሲደርሳት የምትገባበት እንደጠፋት ታስታውሳለች።
መተግበሪያው በርካታ ሙስሊም ሕንዳዊ ሴቶች 'ለሽያጭ' እንደቀረቡ አስመስሎ ፎቷቸውን ለጥፏል። 'የሽያጭ' ድረ ገጽም አለው።
የእነዚህ ሴቶች ፎቶ የተወሰደው ከተለያዩ ገጾች ነው። ከዚያም ለእያንዳንዳቸው የማንነት መግለጫ (ፕሮፋይል) ተዘጋጅቶ 'ለሽያጭ' እንደቀረቡ ሆነው ቀርበዋል።
የመተግበሪያው መነሻ ገጽ ላይ ማንነቷ የማይታወቅ ምስል አለ። ሀና ይህን ምስል አልፋ ወደ ሁለተኛው ገጽ ስትሸጋገር የጓደኞቿን ፎቶ አገኘት። ሦስተኛው ገጽ ላይ ደግሞ የራሷን ምስል።
"83 ስም ነው የቆጠርኩት። ከዚያም በላይ ሊሆን ይችላል። ፎቶዬን ከትዊተር ላይ ወስደው ከስሜ ጋር ለጥፈውታል" ትላለች።
መተግበሪያውን ከማየቷ ከ20 ቀናት በፊት ነበር 'ሥራ' የጀመረው።
"እስከዚያ ቀን ድረስ ስለ ድረ ገጹ አላውቅም ነበር። ሳየው መላ አካላቴ ተረበሸ" ስትል ታስታውሳለች።
"አላማቸው እኛን አሸማቆ ዝም ማስባል ነው"
መተግበሪያው በገጹ ላይ ያሉት ሴቶች 'እንደሚሸጡ' ይጠቁማል። ሴቶቹን ለመግለጽ የተጠቀመው 'ሱሊ' የሚል ቃል ነው። ይህ ቃል ቀኝ ዘመም ሂንዱዎች ሙስሊም ሴቶችን ለማጥላላት የሚጠቀሙበት አስጸያፊ ቃል ነው።
መተግበሪያው የተዘጋጀው የእውነት ሙስሊም ሴቶችን 'ለመሸጥ' ሳይሆን በማንነታቸው ለማንቋሸሽና ለማሳፈር ነው።
ሀና እንደምትለው በሐይማኖቷ ምክንያት ነው ኢላማ የተደረገችው።
"ድምጼን የማሰማ፣ አደባባይ የምወጣ ሙስሊም ሴት ነኝ። አላማቸው እኛን አሸማቆ ዝም ማስባል ነው" ትላለች።
መተግበሪያው የተሠራበትን ድረ ገጽ ያዘጋጀው ጊቲሀብ ቅሬታ ሲቀርብለት መተግበሪያውን ዘግቶታል።
"ከፖሊሲያችን ጋር የሚጻረር መተግበሪያ ስለሆነ አጥፍተነዋል" ሲልም ጊቲሀብ መግለጫ አውጥቷል።
መተግበሪያው ቢዘጋም ፎቷቸው ተለጥፎ የነበሩ ሴቶች አሁንም ድንጋጤ ውስጥ ናቸው።
መተግበሪያው ኢላማ ያደረገው ድምጻቸውን በጉልህ የሚያሰሙ ሙስሊም ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋቾች፣ አርቲስቶች እና ተመራማሪዎችን ነው።
ከእነዚህ መካከል የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸውን ለመዝጋት የተገደዱ ሴቶችም አሉ። በቀጣይም ወከባ ይደርስብናል ብለው የፈሩ ጥቂት አይደሉም።
ፎቷቸው በመተግበሪያው ከተለጠፈ ሴቶች አንዷ "ምንም ያህል ብርቱ ሴት ብትሆኚ ፎቶሽና የግል መረጃሽ ለሕዝብ ይፋ ሲደረግ ይረብሻል" ስትል ስሜቷን ገልጻለች።
አብዛኞቹ ሴቶች ከዚህ መተግበሪያ ጀርባ ናቸው የተባሉትን ግለሰቦች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እያጋለጡ ነው። ትግላቸውን እንደሚቀጥሉም ይናገራሉ።
ሴቶቹ ዋትስአፕ ላይ የቡድን መልዕክት መለዋወጫ ከፍተው እርስ በእርስ እየተደጋገፉ ነው። ለፖሊስም አቤት ብለዋል።
ሀና የዋትስአፕ ቡድኑ አባል ናት።
"ከአምስት እስከ አሥር ሩፒ ሴቶችን ሲጫረቱ ነበር"
ታዋቂ የመብት ተሟጋቾችና መሪዎች ሙስሊም ሴቶቹ የደረሰባቸውን በመቃወም ድምጻቸውን አሰምተዋል።
ፖሊስ ጉዳዮን እየመረመረ ይገኛል። መተግበሪያውን በመሥራቱ እጃቸው ያለበት እነማን እንደሆኑ ይፋ ከማድረግ ግን ተቆጥቧል።
መተግበሪያውን የሠሩት ሰዎች ማንነታቸውን መደበቅ ችለዋል። ገጹን የከፈቱትም በሐሰተኛ ስም ነው።
የተቃዋሚው ኮንግረስ ፓርቲ የማኅበራዊ ሚዲያ አስተባባሪ ሀሺባ አሚን እንደምትለው፤ "ከመተግበሪያው ጀርባ ያሉት ሙስሊሞችን፣ በተለይ ደግሞ ሙስሊም ሴቶችን በማጥላላት የሚታወቁ ናቸው" ትላለች "በቀኝ ዘመም ፖለቲካቸውም ይታወቃሉ።"
ሀሺባ እንደምትለው ሙስሊም ሴቶች ላይ ጥቃት ሲሰነዘር የመጀመሪያው አይደለም።
ኢድ በሚከበርበት ቀን አንድ የዩቲዩብ የቀጥታ ሥርጭት ገጽ ተከፍልቶ "የኢድ ልዩ ሽያጭ" በሚል የሕንድ እና የፓኪስታን ሙስሊም ሴቶች ሲታዩ ነበር።
"ሰዎች ከአምስት እስከ አሥር ሩፒ [የሕንድ ገንዘብ] ሴቶችን ሲጫረቱ ነበር። የሴቶቹን ሰውነት እያነጻጸሩ እንደፍራቸዋለን እያሉ የሚያስፈራሩም ነበሩ" ስትል ሀና ወቅቱን ታስታውሳለች።
ሀሺባ ደግሞ ያን እለት አንድ ማንነቱ ያልታወቀ አካል ትዊተር ላይ ለጨረታ አቅርቧት እንደነበር ትናገራለች። ያ ገጽ አሁን እንዲዘጋ ተደርጓል።
"ሰውነቴን እየሰደቡ፣ ስለ አስጸያፊ ወሲባዊ ድርጊት የሚናገሩ ነበሩ" ስትል ሀና የደረሰባትን ትገልጻለች።
በኢድ ወቅት ትዊተር ላይ 'ለሽያጭ' ያቀረቧት ሰዎች አሁንም ሱሊ ዲልስ በተባለው መተግበሪያ ላይ እንዳወጧት ሀና ታምናለች።
መተግበሪያውን የሠራነው እኛ ነን እያሉ ትዊተር ላይ ሲጽፉ የነበሩ ሰዎች ገጻቸው ታግዷል።
የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት፤ የበይነ መረብ ጥቃት ሴቶችን በማስፈራራት እና በማጣጣል ድምጻቸውን ለማፈን የሚቃጣ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
"እነዚህ ሴቶች አሳዳጃቸው ብዙ ነው"
ከሳምንታት በፊት 200 የሚጠጉ ታዋቂ ተዋንያን፣ ሙዚቀኞች፣ ጋዜጠኞችና የመንግሥት ባለሥልጣናት ፌስቡክ፣ ጉግል፣ ቲክቶክና ትዊተር የሴቶችን ደኅንት እንዲጠብቁ የሚያሳስብ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈዋል።
"ኢንተርኔት የ21ኛው ክፍለ ዘመን አደባባይ ነው። ክርክር የሚካሄደው፣ ማኅበረሰብ የሚገነባው፣ እቃ የሚሸጠው ወዘተ ኢንተርኔት ላይ ነው። ሆኖም ግን ኢንተርኔት ለበርካታ ሴቶች ነፃ ቦታ አይደለም። ብዙ ጥቃቶች እየደረሱ ነው" ይላል ደብዳቤው።
የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት መሠረት፤ ሕንድ ውስጥ በአደባባይ ሐሳባቸውን በግልጽ የሚያሰሙ ሴቶች በዋነኛነት ኢላማ ይደረጋሉ።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ጥቁር ሴቶች በግንባር ቀደምነት የበይነ መረብ ጥቃት ይደርስባቸዋል። ሕንድ ውስጥ ደግሞ ማኅበረሰቡ ጫና የሚያሳድርባቸው ሐይማኖቶች ተከታዮች እና ጎሳዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ይሰነዘራል።
የአምነስቲ የሕንድ ቅርንጫፍ የቀድሞ ቃል አቀባይ ናዚያ ኤሩም እንደምትለው፤ ማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ ሙስሊም ሴቶች ጥቂት ናቸው። እነሱም የበይነ መረብ ጥቃት በተደጋጋሚ ይደርስባቸዋል።
"እነዚህ ሴቶች አሳዳጃቸው ብዙ ነው" ትላለች ናዚያ።
ጥቃቶቹ በተደጋጋሚ የሚሰነዘሩት የተማሩ ሙስሊም ሴቶችን ለማፈን እንደሆነ ታስረዳለች።
"ሙስሊም ጠልነትን በይፋ የሚቃወሙና ሐሳባቸውን በግልጽ የሚሰጡ የተማሩ ሙስሊም ሴቶችን መድረክ ለማሳጣት ነው የሚፈለገው። ሴቶቹን አሳፍሮ ድምጻቸውን ለመቀማት የሚደረግ ሙከራም ነው።"
ሀሺባ እንደምትለው፤ ጥቃት ያደርሱባት የነበሩ ሰዎች አንዳችም የሚፈሩት ነገር የላቸውም። ጥቃት ሰንዝረው ምንም እርምጃ ሳይወሰድባቸው ማምለጥ እንደሚችሉ ማወቃቸው የልብ ልብ እንዲሰማቸው አድርጓል።
የሕንድ ገዢ ፓርቲ ቢጄፒ ደጋፊዎች ሳይቀሩ ሙስሊሞች ላይ የሚደርስ ጥቃትን እንደሚያበረታቱ እንደ ማስረጃ ትጠቅሳለች።
አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን፤ ሙስሊም ዜጋን የገረፉ ስምንት ሂንዱዎች ላይ ሲፈረድ የሰጡትን አስተያየት ሀሺባ ታነሳለች።
በተጨማሪም አዲሱ የሕንድ የብሮድካስት ባለሥልጣን መሪ ሂንዱዎችን "ሙስሊሞች ላይ ተኩሱ" እያሉ ሲቀሰቅሱ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ተለቋል።
ሱሊ ዲልስ የተባለው መተግበሪያ ፎቷቸውን ለጥፎ 'ለሽያጭ' ያቀረባቸው ሙስሊም ሴቶች ፍትሕ ለማግኘት የሚያደርጉት ትግል አታካች መሆኑ አይቀርም።
ነገር ግን የሚበግራቸው ኃይል ያለ አይመስልም። ፍትሕን ከማስፈንም አያፈገፍጉም።
ሀና "ፖሊስ ለሽያጭ ያቀረቡንን ሰዎች የማይዝ ከሆነ ጉዳዩን ፍርድ ቤት እወስደዋለሁ። እስከ መጨረሻውም እታገላለሁ" ትላለች።












