ሴቶች ከአንድ በላይ ባል የማግባት ውዝግብ በደቡብ አፍሪካ

አንዲት ሴትና አራት ወንዶች ያሉበት የሠርግ ኬክ ላይ ያሉ አሻንጉሊቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ሴቶች ከአንድ በላይ ባል ማግባት እንዲችሉ የሚፈቅደውን ሕግ ለማርቀቅ ዕቅድ ማቅረቡን ተከትሎ በርካታ ወግ አጥባቂዎች ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ናቸው።

መንግሥት ፖሊአንድሪ የተሰኘውንና ሴቶች በርካታ ባሎች ማግባት የሚያስችለውን ልምድ ሕጋዊ እውቅና መስጠት ይፈልጋል።

ይህ ተቃውሞ በጉዳዩ ላይ ከፍተኛ ምርምር ያደረጉትን ምሁር ፕሮፌሰር ኮሊስ ማቾኮን አያስገርማቸውም።

ተቃውሞውንም የሚያያይዙት ወንዶች ሴቶችን ለመቆጣጠር ከመፈለጋቸው ጋር ነው።

"የአፍሪካ ሕዝቦች ለእውነተኛ እኩልነት ዝግጁ አይደሉም። መቆጣጠር የማንችላቸውን ሴቶች ምን ማድረግ እንዳለብን ግራ እንጋባለን" ይላሉ።

የደቡብ አፍሪካ ሕገ መንግሥት በዓለም ላይ ሊበራል ከሚባሉትና በርካታ ነገሮችንም የሚፈቅድ ነው። ለምሳሌም ያህል የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ እንዲሁም ወንዶች ከአንድ ሴት በላይ እንዲያገቡ ይፈቅዳል።

የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁና ነጋዴው ሙሳ ምስሌኩ ይህንን ዕቅድ ከተቃወሙት አንዱ ነው። ራሱ አራት ሚስቶች ያሉት ይህ ግለሰብ "ይህ ሁኔታ የአፍሪካን ባህል ያጠፋዋል። ልጆቻቸውስ እንዴት ይሆናሉ? የማንስ ልጅስ መሆናቸው እንዴት ይለያል?" በማለት ሙሳ ይጠይቃል።

ሙሳ ከአራት ሚስቶቹ ጋር ያለውን ህይወት የሚያስቃኝ በደቡብ አፍሪካ ቴሌቪዥን አንድ ፕሮግራም አለው።

"ሴት የወንድን ሚና መተካት አትችልም። ታይቶ ተሰምቶም አይታውቅም። በአሁኑ ወቅት ሴቶች ሎቦላ (ጥሎሽ) ሊሰጡ ነው ማለት ነው? ወንዱ በእሷ ስም ሊጠራ ነው ማለት ነው?" በማለት ይጠይቃል።

በድብቅ እየተፈፀሙ ያሉ ጥምረቶች

ፕሮፌሰር ማቾኮ በትውልድ ቦታቸው ዚምባብዌ 20 ሴቶችንና የእነሱን ባሎች 45 ወንዶችን አናግረዋል። ምንም እንኳን በዚምባብዌም ቢሆን የሴቶች ከአንድ ወንድ በላይ ማግባት ሕጋዊ ፈቃድ ባይኖረውም በምስጢር ይፈጸማል።

"ፖሊአንድሪ በማኅበረሰቡ ውስጥ እንደ ነውር ስለሚቆጠር በርካቶች በምስጢር ነው የሚፈጽሙት" የሚሉት ፕሮፌሰሩ "ድንገት እንኳን እነዚህ ተጣማሪዎች በማያምኑት ወይም በማያውቁት ሰው ቢጠየቁ እንዲህ አይነት ጋብቻ እንዳለ አናውቅም ብለው ይክዳሉ" ይላሉ።

አክለውም "ይህን የሚያደርጉት ሊደርስባቸው የሚችሉ መከራዎችን በመፍራት ነው" ይላሉ።

በፕሮፌሰር ማቾኮ ጥናት ላይ የተካተቱት ግለሰቦች በተለያዩ ቤቶች ቢኖሩም በተለያየ ሁኔታ ተጣምረው ነው ያሉት።

ሙሳ ምስሌኩ ከአራት ሚስቶቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Musa Mseleku

የምስሉ መግለጫ, የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጁና አራት ሚስቶች ያሉት ሙሳ ምስሌኩ (ከመሃል) ሴቶች በርካታ ባል ማግባታቸው "አፍሪካዊ አይደለም"

"አንደኛዋ ሴት እንዳለችው በርካታ ባሎችን የማግባት ፍላጎቷ የመጣው ገና ስድስተኛ ክፍል እያለች በ12 ዓመቷ ነበር። ይህም ንግሥት ንብ በርካታ ባሎችን በቀፎ ውስጥ እንደምትይዝ ስላየች ነው" ይላሉ ፕሮፌሰሩ።

ትልቅም ከሆነች በኋላ ከበርካታ ወንዶች ጋር በተመሳሳይ ወቅት የፍቅር ግንኙነት ማድረግ ጀመረች። ሁሉም ይተዋወቃሉ።

"ከዘጠኙ ባሎቿ አራቱ የመጀመሪያዎቹ የፍቅር ጓደኞቿ ናቸው" ይላሉ።

በፖሊአንድሪ የፍቅር ግንኙነት ውስጥ ግንኙነቱን የሚጀምሩት ሴቶች ናቸው። ሴቷ ወንዶቹንም የትዳር አጋሯ እንዲሆኑ ትጠይቃለች። አንዳንዶች ወንዶች ጥሎሽ የሚከፍሉ ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ ለኑሯዋ የሚያስፈልገውን እንሸፍናለን ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ከባሎቿ ውስጥ ይህንን ጥምረት የሚረብሽ ሰው ከተገኘ እንዲወጣ ይደረጋል። ፕሮፌሰር ማቾኮ እንደሚሉት ወንዶቹ በፖሊአንድሪ ጥምረት ውስጥ መግባት የፈለጉበት ዋነኛው ምክንያት ፍቅር መሆኑን ካናገሯቸው ግለሰቦች መረዳት ችለዋል። ብዙዎቹ ባለቤታቸውንም ማጣት እንደማይፈልጉ ለፕሮፌሰሩ ነግረዋቸዋል።

አንዳንዶቹ ደግሞ ሚስቶቻቸውን በፍቅር ግንኙነት ማርካት ስላልቻሉ ፍቺን ወይም ውስልትናን ለማስወገድ ሲሉ ሌላ ባል እናግባ ሲሏቸው እሺ እንደሚሉ ተናግረዋል።

ሌላኛው የተሰጠው ምክንያት ወንዶቹ መካን በሚሆኑበት ወቅት ሲሆኑ ሌላ ተጨማሪ ባል አግብታ ልጅ እንትወልድም ይስማማሉ። በዚህም ጥምረት በመስማማታቸው ወንዶቹ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ስም እንዳይጎድፍ እንዲሁም "በወንድነታቸው ተዋርደዋል" የሚለውን ስም ያስቀርላቸዋል።

የሐይማኖት አባቶች ቁጣ

ምንም እንኳን በዚምባብዌ ያለውን የፖሊ አንድሪ ልምድ እንዳለ ቢያውቁም በደቡብ አፍሪካ በተመሳሳይ መልኩ ይፈጸም እንደሆነ ፕሮፌሰር ማቾኮ መረጃው የላቸውም።

ነገር ግን የሥርዓተ ፆታ መብት ተሟጋቾች መንግሥት ለፖሊአንድሪ ሕጋዊ ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቀዋል። የአገሪቱ ሕግ አንድ ወንድ ከአንድ ሚስት በላይ ማግባት እንደሚፈቅደው በተመሳሳይ መልኩ ለሴቶችም እኩልነታቸውንና ምርጫቸውን ባከበረ መልኩ ለሴቶቹም ሊፈቀድ ይገባል በማለት ይከራከራሉ።

መንግሥት ረቂቁን ከማጽደቁ በፊት ሕዝብ እንዲወያይባቸው በሚል ካቀረባቸው "ግሪን ፔፐር" ሕጎች መካከከል እንደሆነም ተነግሯል።

ከነጮቹ ጨቋኝ የዘር መድልኦ ሥርዓት መገርሰስ በኋላ በደቡብ አፍሪካ ስር ነቀል የሆነ የጋብቻ ሕግ ለውጥ ሊሆንም ይችላል ተብሏል።

"ማስታወስ ያለብን ግሪን ፔፐር የተሰኘው ይህ የሕግ ማሻሻያ የሰብዓዊ መብቶችን ለማስተካከል ይቻል ዘንድ የቀረበ ነው። ይህንን መርሳት የለብንም" በማለት በሴቶች መብት ላይ የሚታገሉት የሕግ ባለሙያ ቻርሊን ሜይ ይናገራሉ።

"የሕግ ማሻሻያው በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን አባታዊ (ፓትሪያርካል) ሥርዓት ስለሚገዳደር ወይም ከአንዳንዶች ዕይታ ጋር ስለሚቃረን ውድቅ ልናደርገው አይገባም" ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ሙስሊም፣ ሂንዱ፣ አይሁዳውያንና የራስተፈሪያን ጋብቻንም እውቅና እንዲሰጥም በዕቅዱ ተካቷል።

ምንም እንኳን ይህ እውቅና በሚመለከታቸው ማኅበረሰቦች ዘንድ ድጋፍ ቢያገኝም በተለይም ፖሊአንድሪ ሕጋዊ እውቅና ይሰጠው የሚለው ጉዳይ ከሐይማኖት አባት የምክር ቤት አባላት ዘንድ ተቃውሞ ገጥሞታል።

ተቃዋሚ የሆነው የአፍሪካ ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲ መሪ ቄስ ኬኔት መሾ በበኩላቸው "ማኅበረሰቡን ያጠፋዋል" ይላሉ።

"የሆነ ወቅት ላይ አንደኛው ወንድ ከኔ በላይ ሌላኛው ጋር ለምን ታሳልፋለች በሚል በወንዶቹ መካከል ፀብ መፈጠሩ አይቀርም" ይላሉ።

የእስላሚክ አል ጃማህ ፓርቲ መሪ ጋኒየፍ ሄንድሪክስ በበኩላቸው "ልጅ በሚወለድበት ወቅት አባቱን ለማወቅ የዘረ መል (ዲኤንኤ) ምርመራ ግዴታ ሊሆን ነው" በማለት የሚቃውሙበትን መንገድ ይናገራሉ።

የቤተሰቡ ልጆች ናቸው

ሙሳ በበኩሉ ደቡብ አፍሪካውያን የእኩልነትን ፅንሰ ሃሳብ ወደ "ፅንፍ" እንዳይወስዱት ጠይቋል።

"አንድ ነገር በሕገ መንግሥቱ ላይ አለ ማለት ለእኛ ጥሩ ነው ማለት አይደለም" ይላል።

አራት ሚስቶች ያሉት ይህ ግለሰብ ለሴቶችም በተመሳሳይ መልኩ ቢፈቀድ የተለየ የሚያደርገው ምንድን ነው? ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፡

"ብዙዎች በርካታ ሚስቶች በማግባቴና ይህንን አስተያየት በመስጠቴ ግብዝ ይሉኛል። ለኔ ዝም ከምል መናገሪያው ወቅት አሁን ነው ብዬ አምናለሁ" ያለው ሙሳ አክሎም "ማለት የምችለው አፍሪካዊ አይደለም። ማንነታችንን መቀየር አንችልም" ብሏል።

ፕሮፌሰር ማቾኮ በበኩላቸው አፍሪካዊ አይደለም በሚለው አይስማሙም ሴቶች በርካታ ባል የማግባት ባህል (ፖሊአንድሪ) በኬንያ፣ በኮንጎና በናይጄሪያ እንደነበረ ጠቁመዋል። በጋቦን እስካሁንም ድረስ የቀጠለ ሲሆን በሕግም ፍቃድ አለው።

"ክርስትናና ቅኝ ግዛት ወደ አፍሪካ መምጣታቸውን ተከትሎ የሴቶች ሚና በከፍተኛ ሁኔታ ቀነሰ። በጋብቻ ውስጥ ሴቶች እንደ እኩል የመታየቱ ሁኔታ አከተመ። ጋብቻ የመጨቆኛ መሳሪያም መሆን ጀመረ" ይላሉ።

ፕሮፌሰር ማቾኮ በፖሊአንድሪ ጥምረት የተወለዱ ልጆች የአባታቸውን ማንነት አያውቁም የሚለው ስጋት ከአባታዊ ሥርዓት (ፓትሪያርኪ) ጋር የተቆራኘ ነው" ይላሉ።

"የልጆች ጥያቄ ቀላል ነው። በእንደዚህ አይነት ጥምረት የተወለዱ ልጆች የቤተሰቡ ልጆች ናቸው" በማለት ያስረዳሉ።