በካናዳ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ መሆናቸው ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, Toronto Star via Getty Images
በምዕራብ ካናዳ የቀደምት ህዝቦች መኖሪያ ስፍራዎች ላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት እየተቃጠሉ ነው ተብሏል።
በትናንትናው ዕለት ቅዳሜ ሁለት ቤተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል።
ቅድስት አንና ቾፕካ የተሰኙት ቤተ ክርስቲያናት የተቃጠሉት በአንድ ሰዓት ልዩነት ሲሆን ባለስልጣናቱ እንዳሉት ሙሉ በሙሉ ህንፃዎቹ ወድመዋል።
የቤተ ክርስቲያኖቹ ቃጠሎ ሆን ተብሎ ሊሆን ይችላል በሚልም ፖሊስ አጠራጣሪ በሚል ምርመራ ጀምሯል።
ባለፈው ሳምንት ሰኞ ካናዳ የቀደምት ህዝቦችን ብሔራዊ ቀን በምታከብርበት እለት በዚያው ግዛት ላይ ሌላ ሁለት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል።
"ከዚህ ቀደም በተቃጠሉት ሁለት ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም በአሁኖቹ ሁለት ቤተ ክርስቲያናት የተጀመረው ምርመራ ቀጥሏል። እስካሁን ድረስ በቁጥጥር ስር የዋለ የለም" በማለት መርማሪ ጄሰን ባይዳ ተናግረዋል።
በቅርቡ በካናዳ ምልክት የሌላቸውና በመቶዎች የሚቆጠሩ ህፃናትን አፅም የያዙ የጅምላ መቃብር ስፍራዎች ተገኝተዋል።
መቃብሩ የተገባቸው ስፍራዎች በዋነኝነት በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ይመሩ የነበሩና የካናዳ ቀደምት ህዝቦችን ወደ ነጭ ባህል ለማላመድ በሚል የተከፈቱ አስገዳጅ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ናቸው።
እነዚህ ትምህርት ቤቶችም በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ ዘመን ነበሩ። የነዚህ መቃብሮች መገኘት በርካታ የቀደምት ህዝቦችን ያስቆጣ ሲሆን በአገሪቱም ውስጥ በነበሩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች ምርመራ እንዲደረግ ጥያቄ ተነስቷል።
ሎወር ስሚልካሚን የተባሉት የአካባቢው የቀደምት ህዝቦች አስተዳዳሪ ለኪይዝ ክሮው ሚዲያ እንደተናገሩ የቾፕካ ቤተ ክርስቲያን እየተቃጠለ ነው የሚለው የስልክ ጥሪ የደረሰባቸው በትናንትናው ዕለት ጥዋት ነው።
ስልክ ከተደወለላቸው ከግማሽ ሰዓት በኋላ በአካባቢው ሲደርሱ ሙሉ በሙሉ ተቃጥሎ ነበር።
"በጣም ነው ያዘንኩት። ከዚህ ምንም አዎንታዊ ነገር አይገኝበትም። ፈታኝ ነው የሚሆነው" ያሉት አስተዳዳሪው በርካታ የአካባቢው ቀደምት ህዝቦችም የካቶሊክ እምነት ተከታይ እንደሆኑና በቃጠሎውም እንደተበሳጩ ተናግረዋል።
በግንቦት ወር የቴኬኤምሉስፕ ቴ ሴክዌፑምክ ቀደምት ህዝቦች እንዳሳወቀው የ215 ህፃናትን አፅም የያዘ የጅምላ መቃብር በቀድሞ አዳሪ ትምህርት ቤት ተገኝቷል።
የህፃናቱ አፅም የተገኘው ካምሎፕስ ኢንዲያን በተባለ አዳሪ ትምህርት ቤት ሲሆን የተከፈተውም በሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ነው። ትምህርት ቤቱም ከ1890 ጀምሮ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቶ በአውሮፓውያኑ 1978 ተዘግቷል።
በያዝነው ሳምንት ሃሙስ ኮወሰስ ቀደምት ህዝቦች እንዳሳወቁት 751 ህፃናትን አፅም የያዘ የጅምላ መቃብር በሌላ አዳሪ ትምህር ቤት ተገኝቷል።
ማሪቫል የተሰኘው ይህ አዳሪ ትምህርት ቤትንም በበላይነት ያስተዳድረው የነበረው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ነው።
ከአውሮፖውያኑ 1863-1998 150 ሺህ የሚሆኑት እነዚህ ህፃናት ከቤተሰቦቻቸው በአስገዳጅ ሁኔታ ተወስደው በነዚህ ትምህርት ቤቶች ይማሩ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2008 የተቋቋመ አንድ ኮሚሽን እንዳጣራው በርካታዎቹ እነዚህ ልጆች ወደ ትውልድ ስፍራቸው መመለስ እንዳልቻሉና በህዝቡም ላይ የባህል ጭፍጨፋ ተፈፅሟል ብሏል።












