ግብጽ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የናይል ተፋሰስ አገራት ጋር ግንኙነቷን ማደስ ለምን አስፈለጋት?

የግብፅ ወታደራዊ ኃይል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ግብጻዊው ተንታኝ ማግዲ አብደልሃዲ እንደሚሉት በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ የሚገኘውን ግዙፍ ግድብን ተከትሎ ከኢትዮጵያ ጋር እየተባባሰ ባለው ውዝግብ ምክንያት ግብጽ አፍሪካ ውስጥ የዲፕሎማሲ እና ወታደራዊ አቅሟን ለማጠናከር እየሞከረች ነው።

በአውሮፓውያኑ 1875 የተቋቋመው የግብጽ ጂኦግራፊ ሶሳይቲ (ማኅበር) የያዛቸው አንዳንድ ጽሑፎች ግብጽ ከሰሃራ በታች ላለው አፍሪካ የተለየ ፍላጎትና ቦታ እንደምትሰጥ የሚያንፀባርቁ ናቸው።

ከእነዚህ መካከል የግብጽ ደቡባዊ ድንበር በምሥራቅ አፍሪካ ቪክቶሪያ ሐይቅ ድረስ ሆኖ የሚያሳይ ታሪካዊ ካርታ ይገኝበታል።

ማኅበሩ የተመሠረተው ግብጽ የመስፋፋትና በርካታ አገራትን ተቆጣጥራ በራሷ የማስተዳደር ፍላጎት በነበራት ዓመታት ውስጥ ነበር። ሰፋ ያለው የግብጽ ምኞት ሱዳንን በቁጥጥሩ ስር ያዋለ ሲሆን ኢትዮጵያንም የማንበርከክ እቅድም ተነድፎ ነበር። ይህም እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1874 አስከ 1876 ባለው ወቅት ሲሆን በአሳፋሪ ሽንፈትም ተጠናቋል።

ከ70 ዓመታት ገደማ በኋላ ግብጽ በአፍሪካም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የፀረ-ቅኝ ግዛት ትግሎችን በማገዝ የዚያን የመስፋፋት እቅዷን የተሳሳተ ሥራዎች አስተካከለች።

ወደ አረብ-እስራኤል ጦርነቶች መግባቷ ግን ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ጋር የነበራትን ግንኙነት አሻከረ።

ያለፉት ጥቂት ዓመታት ግን በተለይም ከናይል ተፋሰስ አገሮች ጋር አስገራሚ የሆኑ የግንኙነቶች መታደስ የታዩበት ነው።

ግብጽ በባለፉት ወራት ከኡጋንዳ፣ ከኬንያ፣ ከቡሩንዲ፣ ከሩዋንዳ እና ከጂቡቲ ጋር በርካታ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስምምነቶችን ተፈራርማለች።

ግብጽ ቀደም ሲልም ከፍተኛ ስምምነቶች ካሏት ከሱዳን ጋር እንዲሁ በቅርቡ የጦር አውሮፕላኖችን እና ልዩ ኃይልን ያካተተ የጋራ ወታደራዊ ልምምዶችን አካሂዳለች።

የህዳሴ ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ግብጽ የኃይል አውታሯን ከሱዳን ጋር አስስተሳሰራለች። ከዚህም በተጨማሪ ከግብጿ አሌክሳንድሪያ እስከ ደቡብ አፍሪካዋ ኬፕ ታውን የሚዘልቅ የባቡር መስመር ለመዘርጋት ታላቅ ራዕይ ያነገበ ዕቅድ ተይዟል።

ከዚህ የውጭ ፖሊሲ ለውጥ ጀርባ ያለው ቁልፍ ነገር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው አወዛጋቢው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው።

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ባለሙያው ናኤል ሻማ "ግብጽ ከግድቡ ጋር በተያያዘ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ልዩነት ለመፍታት ለረዥም ጊዜ በዲፕሎማሲ ላይ ትተማመን ነበር። ነገር ግን የድርድሩ ስኬት የተሟጠጠ ይመስላል ወይም ለመሟጠጥ ተቃርቧል" ይላሉ።

የድርቅ ፍርሃት

ግብጽ ግንኙነቷን እያጠናከረች መሆኗ ማሳያ ሌላኛዋ ታንዛኒያ ናት። ግብጽ በሩፊጂ ወንዝ ላይ ጁሊየስ ኔሬሬ በተሰኘው የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይዋን እያፈሰሰች ነው። ግብጽ ይህንን ፕሮጀክት እንደ ማሳያ በመውሰድ ለናይል ተፋሰስ አገራት ልማት ከጎናቸው መሆኗን መግለፅ ትፈልጋለች።

ከናይል ውጭ ለመጠጥም ሆነ ለእርሻ የሚውል የውሃ ምንጮች የሌሏት ግብጽ ይህን መሰሉን መልዕክት በመጠቀም የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ቀልብ ለመያዝ እየሞከረች ነው።

የአስዋን ግድብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ግብጽ ኢትዮጵያ የምትገነባውን ግድብ ዝም ብሎ መቃወም ሳይሆን ግድቡ በውሃ ፍሰቱ ላይ ሊያመጣው የሚችለው ተፅእኖ ያስፈራታል።

ለዚያም ነው የግድቡን አስተዳደር በተመለከተ አስገዳጅ የሆነ ስምምነት መፈረም አለበት የምትለው።

ግድቡ የግብጽን ግብርና ሊጎዳ እና ሊታረስ በሚችለው ሰፋፊ መሬቶች ላይ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል ብላ ትሰጋለች፤ ይህም ከፍተኛ ድርቅና ሥራ አጥነትን ያስከትላል። ኢትዮጵያ በበኩሏ የሕዳሴው ግድብ ለልማቷ እና ለሕዝቧ የኤሌክትሪክ አቅርቦት አስፈላጊ እንደሆነ ታስረዳለች።

ከወታደራዊ ማስፈሪያዎች ወደ ንግድ ግንኙነቶች

ግብጽ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ላይ ያሳየችው የውጭ ፖሊሲ የአቅጣጫ ለውጥ ለረዥም ዘመናት ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም ለአንዳንድ ግብጻውያን ግን ዘግይቷል።

"በዘመናዊ ፖለቲካ ውስጥ ያለው ጠመንጃ እና መድፍ ብቻ አይደለም" ሲሉ በእንግሊዝ ዌስትሚኒስተር ዩኒቨርሲቲ ምሁር እና የንግድ ሥራ አማካሪ የሆኑት ዋላ ባሪ ይከራከራሉ።

"እንደ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ ወይም ኡጋንዳ ካሉ አንዳንድ የናይል ተፋሰስ አገሮች ጋር የደኅንነት ስምምነቶች መደረሳቸው ጥሩ ቢሆኑም ግብጽ የምትፈልገውን ያህል አቅም አይሰጣትም" ሲሉም ጽፈዋል።

ጠንካራ የንግድ ትስስር ከወታደራዊ ጡንቻ በበለጠ የላቀ ውጤት ሊያመጣ ይችላል ሲሉ ግብጽ ከዘጠኙ የናይል ተፋሰስ አገሮች ጋር ያላትን አነስተኛ ንግድ ያሳያሉ።

"ከእነዚህ አገራት መካከል ግብጽ አስገዳጅ በሆነ መልኩ የንግድ ልውውጥ እንድታደርግ አይደለም። ለምሳሌ የናይል ተፋሰስ አገራት እጅግ ከፍተኛ ጥራት ያለው ቡና ያመርታሉ። ግብጽ ደግሞ በዓመት ከ 95.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቡና ብታስገባም 95 በመቶው የሚሆነው ከአፍሪካ ውጭ የሚገባ ነው" ይላሉ።

ቡና እያፈላች ያለች ልጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ይህ በእንዲህ እንዳለ በግብጽ ሕዝብ ዘንድ ያለው መንፈስ በተወሰነ መልኩ ጠብ አጫሪነት እየሆነ ነው። የግብጽ አስተዳደር ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ኢትዮጵያ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዲወስዱ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተዋል።

የፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲሲ ደጋፊዎች ጭምር የማይታሰቡ የሚመስሉ ሃሳቦችን መሰንዘር ጀምረዋል።

የግብጽን የውሃ መብቶች ካላስጠበቁ የማስተዳደር መብት የላቸውም በማለትም የግብጽ ሕዝብ አስተያየቱን መስጠት ጀምሯል።

ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረግ ፍጥጫ የማይቀር ሆኖ ከተገኘ በኢትዮጵያ ዙሪያ ያሉ ወዳጆቿን ማብዛቷ በተወሰነ መልኩ ውጤት ያስገኛል ብላ ተስፋ ታደርጋለች።

ግብጽና ሱዳን በግድቡ ዙሪያ የተፈጠረው አለመግባባት የቀጠናው ሠላምና መረጋጋት አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል በማለት ለውዝግቡ መቋጫ እንዲደረግለት ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ወስደውታል።

ጉዳዩ ከዚህ በፊትም የፀጥታው ምክር ቤት ፊት ቀርቦ ወደ አፍሪካ ሕብረት ቢላክም እልባት አላገኘም።

ግብጽም ሆኑ ሱዳን ለውዝግቡ እልባት ላለመኖሩ ኢትዮጵያን ይወቅሳሉ። ግብጽ ድርድሩን የአባይ ወንዞች በብቸኝነት መቆጣጠሯን እንደገና ለማረጋገጥ ድርድሩን ተጠቅማበታለች ስትል ኢትዮጵያ ትከሳለች።

በቅርቡ በሱዳን የተካሄደው የጋራ ወታደራዊ ልምምድ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለዓለም ሁሉ ማስጠንቀቂያ ለመላክ በግልፅ የታሰበ ነው። የህይወት እና የሞት ጉዳይ በሆነው ውሃ ላይ ሁለቱ አገራት ወታደራዊም ሆነ ማንኛውንም አማራጭ ከመጠቀም ወደ ኋላ እንደማይሉ ለማሳየት ያለመ ነው።

ግብጽ ወታደራዊ ስምምነቶችን ከኡጋንዳ፣ ከኬንያ እና ከቡሩንዲ ጋር መድረሷ መልዕክቱን የሚያጠናክረው ይመስላል። ምንም እንኳን እነዚህ አገሮች ቁልፍ ብሔራዊ ጥቅሞቻቸው በማይነካበት ጉዳይ ወደ አካባቢያዊ ጦርነት ስለመግባታቸው መገመት ከባድ ነው።

በግብጽ ያለው የሕዝብ አስተያየት ሁሉም ዲፕሎማሲ በሮች ከተዘጉ አስፈላጊ ከሆነ ወታደራዊ እርምጃን እንደሚደግፍ ብዙም ጥርጥር የለውም።

ይህ ሁኔታ በሱዳን የተለየ ሁኔታ ነው ያለው። ግድቡ ከግብጽ በተለየ መልኩ ሱዳንን ተጠቃሚ ያደርጋታል። ለምሳሌም ያህል በየዓመቱ የሚያጥለቀልቃትን ጎርፍ በመቀነስና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል እንድታገኝ ያደርጋታል።

በታዛቢዎች ዘንድ ያለው ሰፊ መግባባት ግብጽ እና ሱዳን የፖለቲካ ፍላጎት፣ ወታደራዊ ኃይል እና ክህሎት ኖሯቸው ቢቻልም ግድቡን በተወሰነ ደረጃ በመምታት በጥቂት ዓመታት ወደ ኋላ ግንባታውን ለመመለስ መሞከር ችግሩን አይፈታውም።

ይህ ይልቁንም አለመተማመንን በመጨመር የጥንት ቅራኔዎች፣ የብሔራዊ ኩራት እና በቀል ላይ እንደገና ነዳጅ ያርከፈክፋል።