ምርጫ 2013፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁሉን አቀፍ ምርጫ እንዲካሄድ ኦፌኮ ጠየቀ

የኦፌኮ አርማ

የፎቶው ባለመብት, OFC

ከቀናት በፊት ሰኔ 14/2013 ዓ.ም በተደረገው ስድስተኛ ብሔራዊ ምርጫ ያልተሳተፈው የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ በአንድ ዓመት ውስጥ ሁሉን አቀፍ ምርጫ እንዲደረግ ባወጣው መግለጫ ጠየቀ።

ፓርቲው ለአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ የመፍትሔ ሃሳብ ብሎ የሰነዘራቸውን ሦስት ነጥቦችንም ዘርዝሯል።

በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉን አካታች የጋራ መንግሥት እንዲቋቋምና "ያልተሳካ" ብሎ የጠራውን የመንግሥት ተሃድሶ እንዲቀጥል፣ "ሁሉን አካታች ብሔራዊ የመግባባት ድርድር እንዲጀመር" የሚሉ ሃሳቦችን አስፍሯል።

በሦስተኛነትም የጋራ መንግሥቱ በጋራ የሚፈጥር ፍኖተ ካርታ እንዲመቻችና በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሁሉን አቀፍ ነፃ ፍትሃዊና ተቀባይነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድም የሚሉ ሃሳቦችን አቅርቧል።

በብሔራዊ መግባባት ያልታጀበ ምርጫ አገሪቷን ከገባችበት ችግር ውስጥ እንደማያወጣት ደጋግሞ ሲናገር እንደነበር ፓርቲው አስታውሶ ከመንግሥት በኩልም ሰሚ ባለመገኘቱ "የአገራችን ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ እየተሸጋገረ ነው" ብሏል።

ኦፌኮና ኦነግ አመራሮቻው በመታሰራቸው፣ በርካታ ቢሮዎቻቸው በመዘጋታቸው ምክንያት ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

በዚህ ምርጫ ኦፌኮ ተገፍቶ መውጣቱንና "የመላውን ኢትዮጵያ ሕዝቦችን የማይወክል ምርጫ ስጋታቸውንም ከሌሎች ፓርቲዎች ማረጋገጥ" እንደቻሉም አስፍረዋል።

በምርጫ ሂደቱም ውስጥ የታዩ ችግሮችንም ጠቅሶ በተለያዩ ምክንያቶች "ሕዝቡን ያላካተተ ምርጫ" እንደሆነም ኦፌኮ በመግለጫው አካቷል።

ምርጫው እንደታሰበው "የገዥውን ፓርቲ ቀልብ መሳብ ባለመቻሉ" የመራጮች ምዝገባ ሦስት ጊዜ ተራዝሟል ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ ቦርዱ የማያውቃቸው ሰባ ዘጠኝ የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመው መገኘታቸው፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ የምርጫ ክልሎች ላይ ምርጫ አለመካሄዱ የምርጫውን ጉድለት የሚያሳዩ ናቸው ብሏል።

በተጨማሪም "በኦሮሚያ ክልል በመቶዎች በሚቆጠሩ ወረዳዎች ውስጥ ገዥው ፓርቲ ብልጽግና በብቸኝነት መወዳደሩን" አስፍሯል።

በትግራይ ውስጥ ባለው ጦርነት ምርጫ ባለመካሄዱና ሌሎች ምክንያቶችንም በመጥቀስ "ሃምሳ በመቶው ሕዝብ ከምርጫ ውጪ ነው" ብሎታል።

"በምንም ተአምር የአገራችንን ፍላጎቶችን የማያሟላ ምርጫ ማለትም ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትንና ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራቲክ ኢትዮጵያን የማይፈጥር ከሆነ ለሚሊዮኖች የሚሆን ልማትና ብልጽግናን አያመጣም" ብሏል።

ከ37 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በመራጭነት የተመዘገበበት እና 47 ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ያቀረቡበት ብሔራዊ ምርጫ ሰኔ 14/2013 የተካሄደ ሲሆን፤ ምርጫው በፀጥታና በሌሎች ምክንያቶች መካሄድ ባልተቻለባቸውም አካቢዎች ደግሞ ጳጉሜ 1 እንደሚካሄድ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ከነዚህም መካከል በሶማሌ ክልልና ሐረሪ ክልል እንዲሁም በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርጫው በተራዘመባቸው ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ደቡብ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በተወሰኑ የምርጫ ክልሎች ምርጫው እንዲራዘም መወሰኑ ይታወሳል።