አሜሪካዊው በእንቅስቃሴ ላይ ከነበረ አውሮፕላን ዘሎ ወረደ

የሎስ አንጀለስ አየር ማረፊያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሎስ አንጀለስ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ አንድ መንገደኛ ከሚንቀሳቀስ አውሮፕላን ላይ ዘሎ ወርዷል።

መንገደኛው የአብራሪዎቹን በር ለመክፈት ከሞከረ በኋላም ነው ዘሎ የወረደው ተብሏል።

ስሙ ያልተጠቀሰው ይህ መንገደኛ በአውሮፕላኑ የአደጋ ጊዜ መውጫ በርንም ከፍቶ እንደዘለለ የአሜሪካ አቪየሽን አስተዳደር አስታውቋል።

ወዲያውኑም ግለሰቡም በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን የደረሰበት አደጋ ባይገለፅም ወደ ሆስፒታል መወሰዱ ተነግሯል።

የበረራ ሰራተኞች እንደተናገሩት መንገደኛው ከመቀመጫው ተነስቶ ወደ አብራሪዎቹ ክፍል መጠጋቱን ነው።

ከዚያም የአብራሪዎቹን በር በኃይል ካንኳኳ በኋላ በአደጋ ጊዜ መውጫ በሩ ዘሎ እንደወረደ ኤንቢኤስ ዘግቧል።

ባለስልጣናቱ ግለሰቡ ለምን ይህንን እንዳደረገ ምርመራ ከፍተዋል ተብሏል።

ኤምብሬር 175 የተሰኘው ይህ አውሮፕላን ወደ መነሻው እንደተመለሰም ተገልጿል።

ክስተቱ የተፈጠረው በያዝነው ሳምንት አርብ በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከምሸቱ 1፡10 ሲሆን በስካይ ዌስት አየር መንገድ ስር ያለው የዩናይትድ ኤክስፕረስ በረራ ነው ተብሏል።

በረራውንም ወደ ሳልት ሌክ ከተማ እንደነበረም ተነግሯል።

ከዚህ ጋር ተመሳሳይ መሆኑ ባይገለፅም በርካታ ክስተቶች በበረራዎች ላይ መታየታቸው እየተነገረ ነው። በዚህ አመት 3 ሺህ የሚሆኑ አስገራሚ ክስተቶች ተመዝግበዋል።

የአቪየሽን አስተዳደር እንዳስታወቀው ምዝገባ ከጀመረበት ከአውሮፓውያኑ 1995 ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የህግ ጥሰቶችን መመዝገቡን ነው። ከነዚህም ውስጥ በርካታዎቹ በበረራ ላይ ማስክ አናጠልቅም የሚሉ ክርክሮች ናቸው።

ከዚህም በተጨማሪ 394 የሚሆኑት ጉዳዮች ደግሞ በበረራ አስተናጋጆች ስራ ጣልቃ ገብተው አሻፈረኝ ያሉ ናቸው። ይህም ከባለፈው አመት ከተመዘገበው 183 በእጥፍ መጨመሩ ተነግሯል።