‹‹ባል›› የብዙዎችን ሕይወት ይቀይራል የተባለለት የአፍሪካ አዲሱ የቅርጫት ኳስ ሊግ

የአፍሪካ አዲሱ የቅርጫት ኳስ ሊግ

የፎቶው ባለመብት, NBAE/Getty Images

‹‹አፍሪካ፤ መጥተናል፤ ጨዋታው ይጀመር›› በሚሉት ቃላት ነበር ለአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የቅርጫት ኳስ ሊግ ወይም ባል ሴኔጋላዊ ፕሬዘዳንቱ አማዱ ጋሎ ፋል ያስጀመሩት፡፡

የመጀመሪያው የሊጉ ጨዋታ እሁድ በናይጄሪያ እና በሩዋንዳ መካከል ተካሂዶ ናይጄሪያ የመጀመሪያውን ጎል በማስቆጠር ታሪካዊ ብትሆንም ሩዋንዳ ጨዋታውን 83 ለ 60 ረትታለች፡፡

በሜዳዋ እና በደጋፊዎቿ ፊት የተጫወተችው ሩዋንዳ ክፍተኛ ድጋፍ እንደነበራትም ተዘግቧል፡፡

‹‹ይሄ የብዙዎችን ህይወት ይቀይራል፡፡ በመላው አህጉሩ ላሉ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ የሚያስችል እና ሌሎች በርካታ እድሎችን የሚፈጥር ነው›› ሲል የቀድሞው የኤን.ቢ.ኤ ተጫዋች እና አሁን ለናይጄሪያ ተሰልፎ የሚጫወተው ቤን ኡዞ ለቢቢሲ ስፖርት ተናግሯል፡፡

‹‹ይህ የአፍሪካ ኤን ቢኤ ነው፣ እናም በዚህ አህጉር ለሚያድጉ ልጆች ይህ የራሴ ብለው የሚጠሩት እና የመጪውን ግዜ ተጫዋቾች የምናፈራበት ነው›› ሲልም አክሏል፡፡

የሊጉ ጨዋታዎች ከአንድ አመት በፊት እንዲጀመሩ እቅድ ተይዞላቸው የነበረ ቢሆንም በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለ14 ወራት ዘግይቶ ተጀምሯል፡፡

በዚህ የመጀመሪያው የውድድር አመት ከ12 አገራት የሚወጣጡ ቡድኖች የሚወዳደሩ ይሆናል፡፡ አንጎላ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል እና ቱኒዚያ እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡ ቀሪ ስድስት ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታዎችን አድርገው ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡

የዚህ አመት የሊጉ ጫዋታዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት በሩዋንዳዋ ዋና ከተማ በሚገኛው እና 10 ሺህ ሰው በሚይዘው የኪጋሊ አሬና ይካሄዳል፡፡

በእያንዳንዱ ጨዋታም 1ሺህ500 አካባቢ ታዳሚዎች እና ተጋባዥ እንግዳዎች ይከታተሉታል፡፡

በሊጉ 26 ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን እስከ ፍፃሜው ጨዋታ ድረስ ሁለት ሳምንታትን የሚፈጅ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡