ባይደን እስራኤል እና ፍልስጤም የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠየቁ

የእስራኤል ጦር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በእስራኤል እና በፍልስጤም ሚሊሻዎች መካከል ለስምንት ቀናት ያክል በጋዛ የቀጠለው ግጭት እንዲቆም ሁለቱ ኃይሎች የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጠየቁ።

ባይደን ለእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ከግብጽ እና ሌሎች አገራት ጋር በመሆን የሁለቱን አገራት ጠብ ጋብ ለማድረግ እየሰሩ እንደሆነም ነግረዋቸዋል፡፡

አሜሪካ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በሁለቱ አገራት መካከል የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሊያወጣው የነበረውን መግለጫ ባለመስማማቷ አስቁማለች።

ለሁለት ሳምንታት የዘለቀው ግጭት እስካሁን ድረስ 61 ህፃናትን ጨምሮ የ212 ሰዎች ህይወትን በጋዛ ቀጥፏል። እስራኤል ደግሞ 10 ሰዎች ሲሞቱባት ሁለቱ ህፃናት ናቸው።

እስራኤል በጋዛ ተዋጊዎችን ብቻ ነው የገደልኩት ማለቷን የቀጠለች ሲሆን የሲቪል ሰዎች ሞት ካለ እንኳን ሆን ብዬ አይደለም ብላለች።

ሃማስ ግን ይህንን ይቃወማል።

"ባይደን የሲቪል ሰዎችን ደህንነት ለመጠበቅ እስራኤልን አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት እንድታደርግ አበረታተዋል" ሲል የነጩ ቤተ መንግሥት መግለጫ አስነብቧል።

"ሁለቱ መሪዎች ሃማስ እና ሌሎች የአሸባሪ ድርጅቶች ላይ የእስራኤል ወታደራዊ ኦፕሬሽኖችን በተመለከተ ውይይት አድርገዋል" ስልም አክሏል።

በግጭቱ ዓለማ አቀፉ ህብረተሰብ ስጋቱን እየገለፀ ሲሆን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችም የሲቪል ሰዎች ሞት እና የግንባታዎች ብሎም የመሰረተ ልማት መውደም እንዲቆም ግልፅ ጥሪዎች እያደረጉ ይገኛሉ።

የፀጥታው ምክር ቤት እስራኤል የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ እንድታቆም እና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎችን እንድትከተል የሚጠይቀው የተኩስ አቁም ጥሪ መግለጫን አሜሪካ ስታስቆም ይህ ለሶስተኛ ግዜ ነው።

"የኛ ስሌት ይህንን ውይይት ከጀርባ ማካሄድ ነው። እስካሁን ልንወስደው የምንችለው ያለን ገንቢ አማራጭ ነው›› ሲሉ የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ተናግረዋል።