የፕሬዝደንት ባይደን የግብር ሰነዶች ዓመታዊ ገቢያቸው በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን አመለከቱ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ለአሜሪካ መንግሥት ግብር መክፈላቸውን የሚያረጋግጡ የግብር ሰነዶች ይፋ ማድረጋቸውን ዋይት ሐውስ አስታወቀ።
ይፋ የሆኑት የግብር ሰነዶች የጆ ባይደን እና የባለቤታቸው ዓመታዊ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን አሳይተዋል።
እአአ 2020 ባይደን እና ባለቤታቸው በድምሩ በዓመት 607,336 ዶላር ያገኙ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 157,414 ዶላር በግብር መልክ ለመንግሥት ከፍለዋል።
እአአ 2019 ላይ ደግሞ ጥንዶቹ በጋራ በዓመት አግኝተው የነበረው 985,223 ዶላር ነበር።
የባይንደን እና የባለቤታቸው የገቢ ምንጭ ናቸው ተብለው ከተዘረዘሩት መካከል፤ የመጽሐፍት ሽያጭ፣ በተለያዩ መድረኮች ላይ የሚያደርጓቸው ንግግሮች እንዲሁም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ያላቸው ተሳትፎዎች ናቸው።
የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለመንግሥት የሚጠበቅባቸውን ግብር ስለመክፈላቸው የሚያረጋግጥ ሰነድ ይፋ አላደረጉም በሚል መነጋጋሪያ ሆነው እንደነበረ ይታወሳል።
የወቅቱ ፕሬዝደንት ባይደን ግን ባለፉት 22 ዓመታት ግብር የከፈሉባቸውን ዶሴዎች ነው ይፋ ያደረጉት።
ባይደን እና ባለቤታቸው ለፕሬዝደንታዊው ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳ እያደረጉ በነበሩት ዓመት ከጠቅላላ ገቢያቸው 25.9 በመቶ ግብር መክፈላቸውን ዋይት ሐውስ አስታውቋል።
በተመሳሳይ ዓመት 30,704 ዶላር ለ10 በጎ አድርራጊ ድርጅቶች በእርዳታ መልክ ሰጥተዋል።
ይፋ የተደረገው ሰነድ እንደሚያሳየው ከሆነ፤ ጥንዶቹ በጠቅላለው ከ1.2 እስከ 2.88 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት አፍርተዋል።
ባይደን የአሜሪካ ፕሬዝደንት በመሆናቸው ወርሃዊ ደሞዛቸው 400,000 ዶላር ነው። ዲሞክራቱ ፕሬዝደንት በወር ከ400,000 ዶላር በላይ የሚያገኙ ሰዎች ተጨማሪ ግብር እንዲከፍሉ ምክረ ሃሳብ እያቀረቡ ነው።
ይህም መንግሥት የተሻለ ማኅበራዊ አገልግሎት ማቅረብ እንዲችል እና ተጨማሪ የሥራ እድል እንዲፈጥር ይረዳዋል ይላሉ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን።
በተመሳሳይ ምክት ፕሬዝደንት ካማላ ሃሪስ እና ባለቤታቸው ዳግ ኤምሆፍ የባለፈው ዓመት የግብር ሰነዶቻቸውን ይፋ አድርገዋል።
ጥንዶቹ ይፋ ባደረጉት የግብር ሰነድ ላይ ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ1.69 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
ከዚህ ገቢያቸው 36.7 በመቶ በግብር መልክ መክፈላቸውን እና 27 ሺህ ዶላር ደግሞ ለበጎ አድራጎት ድርጅት መለገሳቸውን አመላክተዋል።












