በዩክሬን ሴት የሰራዊት አባላት በ'ሂል' ጫማ ወታደራዊ ትዕይንት ያሳያሉ መባሉ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Ukraine defence ministry
የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ሴት የሰራዊቱ አባላት በሚቀጥለው ወር በሚደረገው ወታደራዊ ትዕይንት ከተለመደው የሰራዊቱ አልባሳት መለዮ ውጭ ከፍ ባለ ረዥም ተረከዝ (ሂል) ጫማ እንዲወጡ ለማድረግ ያቀደው ዕቅድ ቁጣን አስከትሏል።
በምክር ቤቱ የተቃዋሚዎች ፓርቲ ተወካይ ኢርያና ጌራሽቸንኮ እንዳሉት ይህ እኩልነት ሳይሆን ፆተኝነት ነው ብለውታል።
የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት አባል የነበረችው ዩክሬን 30ኛ አመት የነፃነት ቀኗን በዓል ምክንያትም በማድረግ ለሚቀጥለው ወር ወታደራዊ ትዕይንት ያቀደችው።
የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ጫማዎቹ የወታደራዊ መለዮ አካል ናቸው ብለዋል።
የሚኒስቴሩ ውሳኔ በርካታ ዩክሬናውያንን ያስደነገጠ ሲሆን ከምክር ቤት የተውጣጡ አባላትን የያዘ ቡድን መከላከያ ሚኒስትሩ አንድሪ ታራን ይፋዊ የሆነ ይቅርታ እንዲጠይቁ ጥሪ አቅርበዋል።
"ወታደራዊ ሰልፍ በሂል ጫማ በጣም አፀያፊ ነገር ነው" በማለት ቪታሊ ፖርቲንኮቭ የተባለ ጋዜጠኛ በፌስቡክ አስተያየቱን ያሰፈረ ሲሆን አንዳንድ ባለስልጣናት ወደ ኋላ የቀረ የመካከለኛው ዘመን እሳቤ አላቸው ብሏል።
ኢርያና ጌራሽቸንኮ በበኩላቸው ሴት ወታደሮች የሰራዊቱን መለዮ ለብሰው በሂል ጫማ የሚያሳዩ ፎቶዎችን በመጀመሪያ ሲመለከቱ ሃሰተኛ መስሏቸው ነበር።
እሳቸው እንደሚሉት ይህ እኩልነት ሳይሆን ፆተኝነት ነው መስሪያ ቤቱም ለሴቶች የሚሆን የመለዮ ጫማ ዲዛይን ማድረግ ለምን አቃተው በማለትም ይጠይቃሉ።
የዩክሬን የቀድሞ ጦር አዛዥ ማሪያ ቤርሊንስካ በበኩላቸው ወታደራዊ ትዕይንቱ የሰራዊቱን ጥንካሬ የሚያሳይ መሆን ነው ያለበት ነገር ግን በዚህ ያየነው ከፍተኛ የጦር አዛዦችን ስሜት ለመቀስቀስና ለማነሳሳት ያለመ ነው ብለዋል።
የተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ኦሌና ኮንድራትዩክ እንደጠቆሙት ከ13 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ሴቶች በቅርቡ በዩክሬይንና በሩሲያ በሚደገፉት ተገንጣዮች መካከል የተደረገው ጦርነት ተሳትፈዋል።
በአገሪቱ ሰራዊትም የሴቶች ቁጥር ከ31 ሺህ በላይ ሲሆኑ ከነዚህም ውስጥ ከ4 ሺህ በላይ በከፍተኛ ማዕረግ ላይ ያሉ ናቸው።












