'ሂል' ጫማዎች እያበቃላቸው ይሆን?

ሂልና ስኒከር ጫማዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአውሮፓውያኑ 2014 የዓለማችን ታዋቂ ሞዴሎችና ዲዛይነሮች የተሰበሰቡበት ፋሽን ትርኢት ተካሂዶ ነበር። በወቅቱ የተመልካቾችን ቀልብ ገዝቶ የነበረው ሞዴሎቹ የለበሱት ልብስ አልነበረም። ያደረጉት ጫማ እንጂ።

ሁሉም ሞዴሎች ያደረጓቸው ጫማዎች ከ95 ሺ ብር በላይ የወጣባቸው ሲሆን ጫማዎቹን ለመስራትም ከ30 ሰዓታት በላይ ፈጅቷል።

በሚያስገርም ሁኔታ እነዚህ ጫማዎች ሞዴሎች የሚያደርጓቸው የተለመዱት ዓይነት ሂል ጫማዎች አልነበሩም። ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ጥቅም ላይ የሚውሉ 'ስኒከሮች'ን ነበር ሞዴሎቹ ያደረጉት።

ይህ ከሆነ አምስት ዓመታት የተቆጠሩ ሲሆን የ'ስኒከር' ተወዳጅነት እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። እንደውም የሆሊዉድ ተዋናዮችና ታዋቂ ዘፋኞች በትልልቅ ዝግጅቶች ላይ 'ስኒከር' አድርገው እየመጡ ነው።

ታዋቂዋ አሜሪካዊት የቴኒስ ስፖርት ተወዳዳሪ ሴሬና ዊሊያምስ የእንግሊዙ ልዑል ሃሪና ሜጋን ሜርክል ሠርግ ላይ ስኒከር አድርጋ ብዙዎችን አስደምማ የነበረ ሲሆን እንደውም ይግረማችሁ ብላ በእራሷ ሠርግ ላይ ስኒከር አድርጋ ተሞሽራለች።

'ሂል' ጫማዎች እያበቃላቸው ይሆን?

የዛሬ አስር ዓመት አካባቢ ትልልቅ ዝግጅቶች ላይ 'ስኒከር' ጫማዎችን ማድረግ የማይታሰብ የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን ግን ከመለመድም አልፎ እየተዘወተረ ነው።

ስኒከር ጫማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአለባበስ ስርዓትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተቀየረ መጥቷል። ቀለል ያሉና ለእንቅስቃሴ የሚመቹ ጫማዎች ተመራጭ እየሆኑ መጥተዋል። ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ከአርባዎቹ እስከ ስልሳዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሰዎችም ጭምር በእነዚህ ስኒከሮች እየተሳቡ ይመስላል።

ሴቶች ዘነጡ የሚባለው ቆንጆ ቀሚስና ረጅም ሂል ጫማ ሲያደርጉ አልያም ትክክለኛው የሥራ አካባቢ አለባበስ ከሂል ጫማዎች ጋር የተያያዘ ብቻ እንደሆነ ማሰብ እየቀረ መጥቷል ትላለች የፋሽን ዘጋቢዋ ሞርጋን ለኬይር። እንደውም ለውጡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተበራከቱ ከመጡት ሴታዊ እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዘ ነው ትላለች።

ሂል ጫማዎችን ሆን ተብሎ ሴቶች ቀስ ብለው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግና ለመቆጣጠር ሆን ተብሎ በወንዳዊ ስርዓት የተቀረጸ ነው ብለው የሚያምኑ ሴቶች ብዙ ናቸው። የ'ስኒከሮች' እነደዚህ ተወዳጅ መሆን ደግሞ ከዚህ አመለካከት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መጽሃፍ ያሳተመችው ሰመር ብሬናን እንደምትለው 'ሂል' ጫማዎችና ኃይል ተያያዥ ጉዳዮች ናቸው።

''ሂል ጫማዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲተዋወቁ የሚያደርጓቸው ወንዶች ብቻ ነበሩ።'' ትላለች።

ጫማዎቹ ለመጀመሪያ ጥቅም ላይ የዋሉት በ16ኛው ክፍለ ዘመን አውሮፓ ውስጥ ሲሆን ፈረስ የሚጋልቡ ወንዶች ብቻ ነበሩ የሚያደርጓቸው።

ሂል ጫማ ያደረጉ ወንዶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፈረንሳይን ከአውሮፓውያኑ 1643 እስከ 1715 ድረስ የመራው ሉዊስ አስራ አራተኛ በየትኛውም ቦታ ሂል ጫማ ነበር የሚያደርገው። ምክንያቱም ጫማው ለምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ስለማይመች ሥራ እንደማይሰራ ማሳያ ተደርጎ ይቆጠርለት ነበር።

ነገር ግን አሁንም ድረስ ረጅም ሂል ጫማዎችን አድርጎ በሥራ ገበታ ላይ መገኘት ለሴቶች ተቀባይነት ያለው አለባበስ እንደሆነ የሚያስቡ ብዙዎች ናቸው።

በፈረንጆቹ 2016 ትልቅ ድርጅት ውስጥ በእንግዳ ተቀባይነት የምትሰራ አንዲት እንግሊዛዊት ለምን ሂል ጫማ አላደረግሽም በሚል ከሥራዋ ተባርራ ነበር።

ታዋቂው የጣልያን ዲዛይነር ፍራንሴስኮ ሩሶ በ2018 ለሁለቱም ጾታዎች የሚሆን አዲስ የጫማ ዓይነት አስተዋውቋል። ምክንያቱ ደግሞ ሰዎች ስለ ጫማ ሲያስቡ የወንድ የሴት ብሎ ማሰብ ማቆም አለባቸው ብዬ ስለማምን ነው ብሏል።