የጦር ሠራዊቷ ለረሃብና ለችግር የተጋለጠባት ሊባኖስ እርዳታ ጠየቀች

የሊባኖስ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሊባኖስ ጦር ሠራዊት የዓለም ኃያላን አገራት አገሪቱ በገባችበት የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ወታደሮቹ እየተቸገሩ ብሎም እየተራቡ መሆኑን ጠቅሶ እርዳተ እየጠየቀ ይገኛል።

የሊባኖስ ፓውንድ ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ የዋጋውን 90 በመቶ ያጣ ሲሆን ይህም የወታደሮችን ደሞዝ እና የሠራዊቱን በጀት ከጥቅም ውጪ አድርጎታል።

በፈረንሣይ አስተናጋጅነት እየካሄደ ያለው የለጋሽ አገራት ጉባኤ ላይ የቀረበው ጥያቄ የገንዘብ ሳይሆን የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመድኃኒት እና የመለዋወጫ ጥያቄ ነው።

የአገሪቱ ሠራዊት እጅግ በተከፋፈለችው አገር ሊባኖስ ውስጥ ብቸኛ የቀረ ብዙሃኑን የሚያስማማ ብሎም የሚያረጋጋ ኃይል ነው።

ሠራዊቱ በገለልተኝነቱ መልካም ስም ያለው ሲሆን በአገሪቱ ከሚታወቁት 18 ሐይማኖታዊ ቡድኖች ብሎም ካሉት የፖለቲካ ኃይሎች በሙሉ ድጋፍ አለው።

ምዕራባዊያኑም ሠራዊቱን በኢራን የሚደገፈውን ታጣቂው የሺአ እስላማዊ እንቅስቃሴ ቡድን ሂዝቦላህን ለማጥቃት ይጠቀሙበታል።

"የሊባኖስ ሠራዊት በአገሪቱ ያለው የፀጥታ ሁኔታ እንዳይበላሽ ለሚደረገው ጥረት ምሰሶ በመሆኑ ተልዕኳቸውን እንዲወጡ ማገዝ ተቀዳሚ ተግባር ነው" ሲሉ የፈረንሣይ መከላከያ ሚኒስቴር ባልደረባ የሆኑ ባለሥልጣን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የሊባኖስ ጦር አዛዥ ጄኔራል ጆሴፍ አውን በመጋቢት ወር ወታደሮቻቸው "እንደ ሌላው ሕዝብ እየተሰቃዩ እና እየተራቡ ነው" በሚል መግለፃቸውን ተከትሎ ነው ፈረንሳይ ይህንን የለጋሾች ጉባኤ ያዘጋጀችው።

አክለውም የፖለቲካ አመራሩ ባለአደራው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀሰን ዲያብ ባለፈው ነሐሴ በቤሩት ወደብ ላይ ከደረሰው አሰቃቂ ፍንዳታ በኋላ ስልጣናቸውን ከለቀቁ ወዲህ አዲስ ካቢኔ ለመመስረት አለመቻሉን ጠቅሰው ወቀሳቸውን አሰምተዋል።

"ወዴት እንሄዳለን? ምን ለማድረግ አስባችኋል?" ሲሉም ጠይቀዋል።

ባለፈው ማክሰኞ ባደረጉት ንግግርም "እርዳታ ለማግኘት ወደ አጋር መንግሥታት ፊታችንን እንድናዞር ተገደናል፤ ሠራዊቱ በእግሩ ቆሞ እንዲቀጥል እርዳታ ለማግኘት ወደ የትኛው የዓለም ጫፍ ለመጓዝ ዝግጁ ነኝ" ሲሉ ተደምጠዋል።

የሊባኖስ ጦር በተለይም ለወተት፣ ለዱቄት፣ ለሕክምና አቅርቦቶች፣ ለነዳጅ እና ለመለዋወጫ እቃዎች ተለይቶ የተቀመጡ ፍላጎቶች እንዳሉት የፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ በፈረንሳይ የመከላከያ ሚኒሰቴር ውስጥ ያሉ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል።

አሜሪካ ባለፈው ወር ለሠራዊቱ የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ከ15 ሚሊዮን ዶላር ወደ 120 ሚሊዮን ዶላር ከፍ እንደምታደርግ አስታውቃለች ።