ኪም ጆንግ ኡን ሰሜን ኮሪያ ለድርድርም ሆነ ለፍጥጫ መዘጋጀት አለባት አሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ለሚደረግ ውይይት ወይም ፍጥጫ መዘጋጀት ያስፈልጋታል፣ "በተለይም ለፍጥጫ ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ መሆን አለባት" ሲሉ ተናገሩ።
ቀደም ሲል በፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳዳር በኩል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመመስረት የሚደረገውን ጥረት ሰሜን ኮሪያ ችላ ብላው ቆይታለች።
የአሁኑ ፕሬዝዳንት ኪም አስተያየት ግን ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካ ጋር ውይይት ለመጀመር ፍላጎት እንዳለ የሚያሳይ የመጀመሪያው ምልክት ነው ተብሏል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ይህንን ንግግር ያደረጉት ዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ ውስጥ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ነው።
በዚህ ሳምንት በተጀመረው የአገሪቱ ገዢ ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው የምግብ እጥረት እንዳጋጠማት ተናገረዋል።
በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በኩል እንደተዘገበው ኪም ባደረጉት ንግግር ላይ የሰሜን ኮሪያን ሰላምና ደኅንነቷን ለማረጋገጥ እንዲሁም "የአገራችንን ክብር ለመጠበቅና ነጻ የሆነ የልማት ጥቅሟን ለማስከበር በተለይ ለሚገጥመን ፍጥጫ ሙሉ ለሙሉ ዝግጁ መሆን አለብን" ብለዋል።
ጨምረውም ሰሜን ኮሪያ በአካባቢዋ ያለውን ሁኔታ ለማረጋጋትና ለመቆጣጠር "በንቃትና በፍጥነት" ምላሽ ትሰጣለች ሲሉ ተናግረዋል።
በሰሜን ኮሪያው መሪና በአዲስ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት አስተዳደር መካከል ያለው ግንኙነት አሁንም በውጥረት የተሞላ ነው።
ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በኩል የወጣውና ሰሜን ኮሪያን ለዓለም ሰላም "ከባድ ስጋት" እንደሆነች ያመለከተው መግለጫ ቁጣ የተቀላቀለበት ምላሽን ያስከተለ ሲሆን፤ ሰሜን ኮሪያ በሰጠችው ምላሽ ይህ አገላለጽ ባይደን አሜሪካ ስትከተለው የቆውን "የጠላትነት አመለካከት" አጠናክራ ለመቀጠል ያላትን ፍላጎት ያሳያል ብሏል።
በቅርቡ አሜሪካ ከሰሜን ኮሪያ አንጻር ያላትን ፖሊሲ የገመገመች ሲሆን በዚህም የኮሪያ ባሕረ ገብ መሬት አካባቢ ከኒውክሊየር ስጋት ሙሉ ለሙሉ ነጻ እንዲሁን እንደምትጥር አመልክቷል።
ባይደንም ከሰሜን ኮሪያ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት የዲፕሎማሲና የጫና መንገድን እንደሚከተሉ ቃል ገብተዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ አገራቸው በሰሜን ኮሪያ ላይ የምትከተለውን አዲስ ፖሊሲ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ "ወሳኝ በሆነ ድርድርም ሆነ በታጋሽነት ላይ ብቻ የሚቆም አይሆንም" ብለዋል።
ጨምረውም ከዚህ ይልቅ ከሰሜን ኮሪያ ጋር በውጤት የሚመዘን ተግባራዊ የዲፕሎማሲ አቀራረብን እንደሚከተሉ ተናግረዋል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ከቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ሁለት ጊዜ ተገናኝተው የተወያዩ ቢሆንም አካባቢውን ከኒውክሌር ጦር መሳሪያ ነጻ የማድረጉ ንግግራቸው ግን ብዙ ርቀት አልሄደም።
ባለፈው ጥር ወር ላይ ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሲመተ በዓል ቀናት ቀደም ብሎ ኪም አገራቸው ያላትን ኃይልና ጥንካሬ ለማሳየት ግዙፍ የጦር መሳሪያ ትርኢት አሳይተው ነበር።

















