ኪም ጆንግ ኡን ሰሜን ኮሪያ የምግብ እጥረት እንዳጋጠማት አመኑ

ኪም ጆንግ ኡን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን አገራቸው የምግብ እጥረት እንዳጋጠማት በይፋ ተናግረዋል።

የአገራቸው ከፍተኛ የስራ አመራሮች ጋር ለስብሰባ በተቀመጡበት ወቅት "የህዝቡ የምግብ ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተታቸው ነው" ብለዋል።

መሪው እንዳሉት በባለፈው አመት ያጋጠመው የታይፉን አውሎ ንፋስ ከፍተኛ ጎርፍ በማስከተሉ አገሪቱ በእርሻ ዘርፍ ማሟላት የሚገባትን ምርት ማምረት አልተቻለም ብለዋል።

አንዳንድ የወጡ ሪፖርቶችም እንደሚያሳዩት የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ነው። በኤንኬ ኒውስ ሪፖርት መሰረት አንድ ኪሎ ሙዝ 45 ዶላር እየተሸጠ ነው።

ሰሜን ኮሪያ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ድንበሯን ዘግታለች።

በዚህም ምክንያት ከቻይና ጋር ታደርገው የነበረውን ንግድ ጫና ውስጥ ከትቶታል።

ሰሜን ኮሪያ ምግብን ጨምሮ፣ ማዳበሪያና ነዳጅ ከቻይና ነው የምታስመጣው።

ከዚህ በተጨማሪ በኒውክሊየር ፕሮግራሞቿ ጋር በተያያዘ አራት አለም አቀፍ ማዕቀቦች ጋር እየታገለች ትገኛለች።

በአገሪቷ ፈላጭ ቆራጭ ናቸው የሚባሉት መሪ በፓርቲያቸው የሰራተኞች ፓርቲ ማዕከራዊ ስብሰባ ላይ ነው ይህንን የተናገሩት።

በዚሁ ስብሰባ ላይ መሪው እንደተናገሩት የኢንዱስትሪ ምርቶች በሚታዩበት ወቅት ከባለፈው ሩብ አመት ጋር ሲነፃፀር ያሁኑ ጨምሯል።

ባለስልጣናቱ ሰሜን ኮሪያ ከአሜሪካና ከደቡብ ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙት ይወያያሉ የተባለ ቢሆንም ከዚህ ጋር ተያይዞ ምንም አይነት መግለጫ አልተሰጠም።

በሚያዝያ ወር ላይ ኪም አገራቸው አርዱስ ማርች ተብሎ እንደሚጠራው ረሃብ እንዳያጋጥማት ህዝባችንን ልንረዳ ይገባል ብለው ነበር።

አርዱስ ማርች ተብሎ የሚታወቀው በሰሜን ኮሪያ ክፉ የረሃብ ዘመን ሲሆን ይህም በአውሮፓውያኑ 1990 ወቅት ነው።

የሶቭየት ህብረት መፈራረስ አገሪቱን አስፈላጊ የሚባሉ እርዳታ እንዳታገኝ አድርጓታል።

በወቅቱ በረሃብ የሞቱ ሰሜን ኮሪያውያን ቁጥር በትክክል ባይታወቅም እስከ 3 ሚሊዮን ይገመታል።