ኮቪድ-19፡ አሜሪካ የተከተቡ ሰዎች ከቤት ውጪ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አይጠበቅባቸውም አለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ሙሉ ክትባቱን የወሰዱ አሜሪካውያን ከቤት ውጪ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንደማይጠበቅባቸው አስታወቀ።
ተቋሙ ባወጣው አዲሱ መመሪያ፤ የሚጠበቅባቸውን ክትባት የወሰዱ ሰዎች ብቻቸውን አሊያም በተከተቡ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ሰዎች መካከል ሲሆኑ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛቸውን ማውለቅ ይችላሉ ብሏል።
ይሁን እንጂ ሲዲሲ በቤት ውስጥና በርካታ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው ቦታዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንደሚገባ መክሯል።
እስካሁን ከ95 ሚሊየን በላይ አሜሪካውያን ሙሉ ክትባቱን ወስደዋል።
ሲዲሲ ማክሰኞ ዕለት የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን አዲሱን መመሪያ "አስገራሚ ለውጥ" ሲሉ አሞካሽተውታል።
ፕሬዚደንት ጆ ባይደን "ተመራማሪዎቻችን የተከተቡ ሰዎች ቫይረሱን ከሌሎች ሰዎች የመቀበል ወይም የማስተላለፍ እድላቸው አነስተኛ እንደሆነ በመረጃ ላይ ተመስርተው አምነዋል። ሁኔታው ግልጽ ነው፤ ከተከተባችሁ ከዚህ በላይም ማድረግ ትችላላችሁ" ብለዋል።
ፕሬዝደንቱ ክትባቱን መውሰድ 'ጀግንነት' ነው ሲሉም ክትባቱን ያልወሰዱ አሜሪካውያን ክትባቱን እንዲወስዱ አሳስበዋል።
"ክትባቱ የእናንተንም ሆነ በዙሪያችሁ ያሉ ሰዎችን ሕይወት እየታደገ ነው። ወደ ቀደሞው እንቅስቃሴያችን እንድንመለስም እየረዳን ነው" ሲሉ ሰዎች ክትባቱን እንዲወስዱ አበረታተዋል።
የጤና ባለሥልጣናቱ ይህንን አዲሱን የጤና መመሪያ ለዋይት ሐውስ የኮሮናቫይረስ ግብረ ኃይል አቅርበዋል።
የሲዲሲ ዳሬክተር የሆኑት ዶ/ር ሮቼል ዋልንስካይ "የተከተቡ ሰዎች ከቤት ውጪ በሚደረጉ አነስተኛ እና መካከለኛ የሰዎች ስብስብ ውስጥ ያለ አፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መገኘት ይችላሉ" ብለዋል።
ይህም ከቤት ውጪ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግንና መመገብ ይጨምራል።
ዳሬክተሯ አክለውም ከቤት ውጪ በሚደረጉ ትላልቅ የሰዎች ስብስቦች ውስጥ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ አለማድረግን በተመለከተ ቦታው ምን ያህል አየር ያስገባል በሚለው እንዲሁም በሰዎች መካከል በሚኖረው የቦታ ስፋት እንደሚወሰን ተናግረዋል።
ይህ መመሪያ የወጣው ሙሉ ክትባቱን ለወሰዱ ሰዎች ነው።
ምንም እንኳን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከቤት ውጪ ሊከሰት ቢችልም፤ ከሰው ወደ ሰው የመተላለፍ እድሉ ግን በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከዚህ ቀደም የተሰራ አንድ ጥናትም ሙሉ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች ቫይረሱን የማስተላለፍ እድላቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
ዳሬክተሯ ዋለንስካይ እንዳሉት የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አጠቃቀም መመሪያው ሙሉ ክትባቱን ለወሰዱ ሰዎች በሰፊው የታቀደው፤ ያልተከተቡትን ለመጠበቅ ሲባል ነው።
"በመሆኑም ያልተከተቡ ሰዎች ከሰዎች ጋር ያላቸውን መሰባሰብ እንዲቀንሱ፣ መሰረታዊ የሆኑ መመሪያዎችን ማለትም ባሉበት አካባቢ በቂ ንጹህ አየር እንዲገባ እንዲያደርጉ እና አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ እንፈልጋለን" ብለዋል ዳሬክተሯ።
እንደ ሲዲሲ ከሆነ እስካሁን ወደ 141 ሚሊየን የሚጠጉ አሜሪካውያን ቢያንስ አንዱን ክትባት ወስደዋል። ይህ ቁጥር የጠቅላላ ሕዝቧን 42 በመቶ ይይዛል።












