ኮሮናቫይረስ፡ ጾም ላይ ያሉ ሙስሊሞች የኮቪድ-19 ክትባት መውሰድ ይችላሉ?

እየተከተበች ያለች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የእስልምና አስተማሪዎችና የጤና ባለሙያዎች ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ጾም ምክንያት የኮቪድ-19ን ክትባት ሳያገኝ እንዳይቀር ማሳሰቢያ እየሰጡ ነው።

በረመዳን ጾም ወቅት በርካታ ሙስሊሞች በቀን ምግብና መጠጥ ከመውሰድ ይቆጠባሉ።

የእስልምና አስተምህሮ ሕዝበ ሙስሊሞ ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መጥለቂያ ድረስ ባለው ጊዜ "ማንኛውም ወደ ሰውነት የሚገባ ነገር ከመውሰድ እንዲቆጠብ" ያስተምራል።

ነገር ግን በሊድስ ከተማ ኢማም የሆኑት ቃሪ አሲም ክትባቱ በጡንቻ በኩል የሚገባ እንዲሁም ምንም ዓይነት የምግብም ሆነ የመጠጥ ንጥረ ነገር ስለሌው ጾም እንደ መግደፍ አይቆጠርም ይላሉ።

"በርካታ የእስልምና አስተማሪዎች በረመዳን ወቅት መከተብ ጾምን መግደፍ እንዳልሆነ ነው የሚገነዘቡት" ሲሉ የብሔራዊ መስጅዶችና ኢማሞች አማካሪ ቦርድ መሪ የሆኑት አሲም ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ነገር ግን በምሥራቅ ለንደን የሕክምና ዶክተር የሆኑት ፋርዛና ሁሴን ሙስሊሞች በቀንም ቢሆንም መጥተው መከተብ ይችላሉ ይላሉ።

"በርካታ ሙስሊሞች በጾም ወቅት የኮቪድ-19 ክትባትን መውሰድ ይገባናል ወይ የሚለው ጉዳይ እንዳሳሰባቸው እንረዳለን" ይላሉ ዶክተሯ።

"በርካታ ጿሚዎች በረመዳን ወቅት መርፌ መወጋት ጾምን መግደፍ እንደሆነ ያምናሉ። ነገር ግን ይህ እውነት አይደለም። ምክንያቱም ክትባት ምንም ዓይነት የምግብ ይዘት የለውም።"

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ያሉ አንዳንድ መስጂዶች ጾም ላይ ሙስሊሞች በረመዳን ወቅት ክትባት ማግኘት እንዲችሉ በማሰብ ክትባት በቅጥር ግቢያቸው መስጠት ጀምረዋል።

በርካታ ብሪታኒያዊያን በክትባት ላይ ያላቸው እምነት ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ክትባቱን ለመከተብ እያዘጋጀች ያለች ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ኢፕሶስ ሞሪ የተሰኘ መረጃ ሰብሳቢ ድርጅት ባሰባሰበው ቁጥር መሠረት ነጭ ያልሆኑ ብሪታኒያዊያን በክትባት ላይ ያላቸው እምነት ባለፈው ጥር ከነበረው 77 በመቶ አሁን ወደ 92 በመቶ ጨምሯል።

በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ ያለው የረመዳን የጾም ወር ባለፈው ሰኞ ጨረቃ በመካ መዲና ላይ ከታየች ጀምሮ ገብቷል።

ወሩ ከንጋት እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ በሚደረግ ጾም እንዲሁም ሰብሰብ ተብሎ በሚደረግ ፀሎትና ስግደት ይታሰባል።

ከዚያም ቤተሰብና ዘመድ አዝማድ ተሰባስቦ ጾሙና በምግብና በመጠጥ ይፈታል።

ረመዳን ለወትሮው እንዲህ ባለው ባሕል ነበር የሚዘከረው። ነገር ግን ዘንድሮና አምና በኮሮናቫይረስ ምክንያት ነገሮች ተቀያይረዋል።

ምንም እንኳን ተሰባስቦ መስገድ ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ይፈቀድ እንጂ ሰዎች ተራርቀው እንዲሰግዱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

አልፎም በሽታው እንዳይዛመት በመስጋት የአንድ ቤተሰብ አባላት ከሌሎች ጋር እንዳይቀላቀሉ ተከልክሏል።

የብሪታኒያ ኢስላሚክ ሜዲካል ማኅበር በረመዳን ወቅት መስጂዶች እንዴት ሰዎችን ማስተናገድ እንዳለባቸው የሚጠቁም መመሪያ አውጥቷል።

ማኅበሩ ታራዊህ [የአመሻሽ ፀሎት] እንዲቀጥል ያሳሰበ ሲሆን ነገር ግን አየር በሚገባት ሁኔታ ያልተራዘመ እንዲሆን መክሯል።

አልፎም ማኅበሩ ኢማሞች ሕዝበ ሙስሊሙን ለመጠበቅ ሲባል ሁለት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ደርበው እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።