በዓለም ዙሪያ በኮሮናቫይረስ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዓለም ዙሪያ በኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሦስት ሚሊዮን ማለፉን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ገለጸ።
ይህ የተገለጸው የዓለም ጤና ድርጅት "ዓለም ወደ ከፍተኛው የኢንፌክሽን መጠን እየተቃረበ ነው" መሆኑን ባስጠነቀቀ ማግስት ነው።
ብዙ ሰዎች በቫይረሱ በመያዝ ሁለተኛ የሆነችው ሕንድ ዛሬ ቅዳሜ ብቻ ከ230,000 በላይ አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን አስመዝግባለች።
ወረርሽኙ ከተከሰተ ወዲህ ወደ 140 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም አርብ ዕለት "በበሽታው የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በአሳሳቢ ደረጃዎች እየጨመረ ነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አክለውም "ባለፉት ሁለት ወራት በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳምንት በቫይረሱ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ ሊጨምር ችሏል" ብለዋል።
ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ እንደገለጸው አሜሪካ፣ ሕንድ እና ብራዚል ከፍተኛ ቁጥር ያስመዘገቡ አገራት ሲሆኑ በሦስቱ አገራት ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሞተዋል።
ባለፈው ሳምንት በዓለም ዙሪያ በየቀኑ በአማካይ 12,000 ሰዎች መሞታቸውን የኤኤፍፒ ዜና ወኪል ዘግቧል።
ይህ ስለወረርሽኙ የሚወጣው አሃዝ በዓለም ዙሪያ በብዙ አገሮች ውስጥ ስላለው የበሽታው ሁኔታ ትክክለኛውን መረጃ ላያንፀባርቅ ይችላል ተብሏል።
በሕንድ ምን እየተከሰተ ነው?
እስከ ጥቂት ሳምንታት በፊት ድረስ ሕንድ በአንጻራዊ ሁኔታ ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ያዋለች ይመስል ነበር። በጥር እና በየካቲት ወራት በአብዛኛው በቀን ከ20 ሺህ በታች አዳዲስ ታማሚዎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ ይህም ከ1.3 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት አገር ዝቅተኛ ቁጥር ነው።
በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ ሄዶ ቅዳሜ ብቻ ለሦስተኛ ተከታታይ ቀን ክብረ ወሰን የሆነ 234,000 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ሪፖርት ተደርጓል።
ሆስፒታሎች የአልጋና የኦክስጂን እጥረት እያጋጠማቸው ነው። የታመሙ ሰዎች ወደ ቤት እየተመለሱ ሲሆን አንዳንድ ቤተሰቦች የሚፈልጉትን መድኃኒት ለማግኘት ወደ ጥቁር ገበያ ፊታቸውን አዙረዋል።
በቢቢሲ የምርመራ ዘገባ መሠረት በሕንድ ውስጥ መድኃኒት ከመደበኛው ዋጋ በአምስት እጥፍ ለገበያ እየቀረበ ነው።
ባለሥልጣናት ወረርሽኙን ለመግታት በዋና ከተማዋ ደልሂ እና በሌሎች አካባቢዎች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የእንቅስቃሴ እገዳዎች ተጥለዋል።
















