ኮሮናቫይረስ ፡ ሕፃናትን አያጠቃም የሚባለው ኮሮናቫይረስ በርካቶቹን እየገደለ ነው

የፎቶው ባለመብት, JESSIKA RICARTE
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ከአንድ ዓመት በላይ ሲሆነው በብራዚል የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል።
በኮቪድ -19 ህይወታቸው የሚያልፍ ሕፃናት እምብዛም እንደሆነ ማስረጃዎች ቢኖሩም በብራዚል ግን 1,300 ሕፃናት በቫይረሱ ሞተዋል።
አንድ ሐኪም የጄሲካ ሪካርቴን የአንድ ዓመት ልጅ የቫይረሱ ምልክቶች የሉትም በማለት የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርግ ፈቃደኛ አልሆነም ነበር። ከሁለት ወር በኋላ ግን በበሽታው ምክንያት በተፈጠረ ችግር ህይወቱ አለፈ።
መምህርት ጄሲካ ሪካርቴ ለሁለት ዓመታት ያደረገችው የማርገዝ ሙከራ ባለመሳካቱ ልጆች አይኖሩኝም ብላ ተስፋ ቆርጣ ነበር። በኋላ ግን ሉካስን ፀነሰች።
"ስሙ የመጣው ከብርሃን ነው። እሱም የህይወታችን ብርሃን ነበር። ደስታችን ከገመትነው እጅግ የላቀ መሆኑን አሳይቶናል" ትላለች።
ሁሌም ጥሩ የምግብ ፍላጎት የነበረው ሉካስ ፍላጎቱን ሲያጣ አንድ ነገር እንደተፈጠረ ተጠራጠረች።
መጀመሪያ ላይ ጥርስ እያወጣ ይሆን ብላ ጄሲካ አስባ ነበር። የሉካስ የክርስትና እናት ነርስ ስትሆን የጉሮሮ ህመም ሊሆን ይችላል የሚል ሃሳብ ሰጠች። በኋላም ትኩሳት፣ ከዚያም ድካም ቆይቶም ለመተንፈስ በመቸገሩ ጄሲካ ወደ ሆስፒታል ወስዳ የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያደርግ ጠየቀች።
"ሐኪሙ የኦክስጅን መጠኑን ለካ። ፣ የሉካስ ኦክስጅን 86 በመቶ ነበር። ይህ ማለት ትክክለኛ እንዳልሆነ አውቃለሁ" ትላለች ጄሲካ።
ትኩሳት ስላልነበረው ሐኪሙ "አትጨነቂ። የኮቪድ-19 ምርመራ አያስፈልገውም። ምናልባት ትንሽ የጉሮሮ ህመም ብቻ ሊሆን ይችላል" ይላታል።
ኮቪድ-19 በልጆች ላይ መገኘቱ እምብዛም መሆኑን ለጄሲካ ነግሮ ጸረ ተህዋሲ መድኃኒቶችን ሰጥቶ ወደ ቤቷ ላካት። ጥርጣሬ ቢኖራትም ሉካስን በግል እንዲመረመር የማድረግ አማራጭ አልነበራትም።
ለ10 ቀናት የተሰጠውን አንቲባዮቲክ ሲጨርስ የተወሰኑት ምልክቶቹ ጠፉ። ድካሙ ግን እንደቀጠለ ሲሆን ይህም የኮሮናቫይረስ ጉዳይ ጄሲካን አሳሰባት።
"ለክርስትና እናቱ፣ ለወላጆቼ፣ ለአማቴ በርካታ ቪዲዮዎችን ልኬ ነበር። ሁሉም ሰው እያጋነንኩ እንደሆነ ነው የሚያስበው። ብዙ እንዳስብ ስለሚያደርገኝ ዜና ማየቴን ማቆም እንዳለብኝ ይነግሩኛል። እኔ ግን ልጄ ልክ እንዳልሆነ አውቅ ነበር። አተነፋፈሱም ትክክለኛ አልነበረም" ትላለች።
ይህ ግንቦት 2020 ነበር። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየጨመረ ነበር። በሰሜን ምሥራቅ ብራዚል ሴአራ በተባለችው መኖሪያ ከተማዋ ታምቦሪል ሁለት ሰዎች ህይወታቸው አልፏል። በከተማዋ ሁሉም ሰው ይተዋወቃል። በከተማው ድንጋጤ ተፈጠረ።"
የጄሲካ ባለቤት የሆነው እስራኤል በበኩሉ በድጋሚ ወደ ሆስፒታል ቢሄዱ እርሷ እና ሉካስ በቫይረሱ የመያዝ ዕድላቸውን ይጨምረዋል የሚል ስጋት አድሮበታል።
ሳምንታት ሲያልፉ ሉካስ የበለጠ እንቅልፋም ሆነ። በመጨረሻም በጎርጎሮሳዊያኑ ሰኔ 3 ቀን ሉካስ ምሳ ከበላ በኋላ ምግቡ ሊረጋለት አልቻለም። ጄሲካ ፈጥና እርምጃ መውሰድ እንዳለባት አወቀች።
በአካባቢያቸው ወደሚገኘው ሆስፒታል ተመለስው ሄዱ። ሐኪሙ ሉካስን የኮቪድ-19 ምርመራ አዘዘለት።
እዚያ የምትሠራው የሉካስ የክርስትና እናትም ውጤቱ ፖዘቲቭ መሆኑን ለባልና ሚስቱ ገለጸች።
ጄሲካ በበኩሏ "በወቅቱ ሆስፒታሉ እንኳን አስታዋሽ አልነበረውም" ትላለች።
ሉካስ ራቅ ብሎ ወደሚገኘው የሕፃናት ክፍል ተዛውሮ የተለያየ የሰውነት ክፍል መቆጣት (መልቲ ሲስተም ኢንፍላማቶሪ ሲንድረም -ኤም አይ ኤስ) ተብሎ በሚጠራ በሽታ ተያዘ።

የፎቶው ባለመብት, JESSIKA RICARTE
ኤክስፐርቶች እንደሚናገሩት ልጆች በኮሮናቫይረስ ከተያዙ እስከ ስድስት ሳምንታት ድረስ የሚመጣው ህመም ብዙም ያልተለመደ ነው።
የሳኦ ፖሎ ዩኒቨርስቲ ባልደረባው ዶ/ር ፋቲማ ማሪንሆ እንደሚሉት በወረርሽኙ ወቅት የኤምአይኤስ ቁጥር ከፍተኛ ሆኗል። ምንም እንኳን ለሁሉም ሞት ምክንያት ባይሆንም።
ጄሲካ ልጇ ሉካስ በነበረበት ክፍል ውስጥ እንድትቀመጥ አልተፈቀደላትም። ራሷን ለማረጋጋት አማቷ ዘንድ ደወለች፡።
"ማሽኑ እስኪቆም ድረስ የማሽኑን ድምጽ እንሰማ ነበር። ይህ የሚሆነው ሰው ሲሞት መሆኑን እናውቃለን። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ማሽኑ እንደገና መሥራት ሲጀምር ማልቀስ ጀመርኩ።"
ሐኪሙ ሉካስ የልብ ድካም እንደገጠመው ከነገራት በኋላ ግን ሊያነቁት ችለዋል።
በሆስፒታሉ ሉካስን ከአንድ ወር በላይ ያከሙት የህጻናት ሐኪሟ ዶ/ር ማኑላ ማኑዌል ሞንቴ አስጊ ሁኔታ ስላልነበረው የሉካስ ሁኔታ በጣም ከባድ መሆኑ ግርምትን ፈጥሮባቸዋል።
በግዛቱ ዋና ከተማ በፎርታሌዛ በአልበርት ሳቢን የህፃናት ሆስፒታል ባለሙያ የሆኑት ሎሃንና ታቫረስ እንደሚሉት በኮቪድ-19 የሚጎዱት አብዛኞቹ ህጻናት እንደ ስኳር፣ የልብና የደም ቧንቧ በሽታ ያሉ ነባር ሁኔታዎች ወይም ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው ናቸው።
ሉካስ ግን እንደዚያ አልነበረም።
በ33 ቀናት ውስጥ ሉካስ በጽኑ ሕክምና ክፍል በነበረ ጊዜ ጄሲካ ለማየት የተፈቀደላት ሦስት ጊዜ ብቻ ነበር። ሉካስ ልቡን ለማከም በጣም ውድ ነው የሚባለውን ኢሞኖግሎቡሊን አስፈለገው።፣
እንደ ዕድል ሆኖ ለራሱ ገዝቶ የተረፈው አንድ ግለሰብ ለሆስፒታሉ ይለግሳል። ሉካስ በጣም ስለታመመ ለሁለተኛ ጊዜ ኢሞኖግሎቡሊን ተሰጠው። ሰውነቱ ሽፍታ በመፈጠሩ የማያቋርጥ ትኩሳት ጀመረው። ለመተንፈስም ድጋፍ አስፈለገው።
ሉካስ መሻሻል ሲያሳይ ሐኪሞቹ የኦክስጂን ቱቦውን ለማውጣት ወሰኑ። ራሱን አውቆ እንዳገገመ ብቸኝነት እንዳይሰማው ጄሲካ እና እስራኤልን በቪዲዮ ደውለው አገናኙት።
"ድምፃችን ሲሰማ ማልቀስ ጀመረ" ትላለች ጄሲካ።
ልጃቸው ምላሽ ሲሰጥ ሲመለከቱ ለመጨረሻ ጊዜ ነበር። በሚቀጥለው የቪዲዮ ጥሪ ወቅት አካሉን ለማንቀሳቀስ የመቸገር ምልክት አሳየ። ከዚያም በሲቲ ስካን በተደረገለት ምርመራ ሉካስ ስትሮክ እንዳጋጠመው አወቀ።
ሉካስ ትክክለኛውን እንክብካቤ ካገኘ እንደሚያገግም ለባልና ሚስቱ ከተነገራቸው በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከጽኑ ህሙማን ክፍል እንደሚወጣ ይጠብቁ ነበር።
ጄሲካ እና እስራኤል ሊጎበኙት በሄዱ ወቅት ሐኪሟም እንደነርሱ ተስፋ ነበራት ትላለች።
"የዚያን ዕለት ምሽት ላይ የሞባይሌን ድምጹን አጠፋሁት። ሉካስ አፍንጫዬን ሲስመኝ በህልሜ አየሁ። ህልሙ ታላቅ የፍቅር፣ የምስጋና ስሜት ስለነበር በጣም ተደስቼ ከእንቅልፌ ነቃሁ። ሞባይሌን ስመለከት ሐኪሙ ያደረጋቸውን 10 ጥሪዎች አገኘሁ።"
ሐኪሟ የሉካስ የልብ ምት እና የኦክስጂን መጠን በድንገት እንደቀነሰና ማለዳ ላይ ማሩን ለጃሲካ ነገረቻት።
ሉካስ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ የኮቪድ-19 ምርመራ ቢደረግለት ኖሮ በሕይወት እንደሚቆይ እርግጠኝነት ይሰማታል።
"ሐኪሞች ኮቪድ-19 አይደለም ብለው ቢያምኑም ህይወት ለማዳን ምርመራውን ማድረጋቸው አስፈላጊ ነው" ትላለች።
"ህጻናት የሚሰማቸውን አይናገሩም ስለዚህ በምርመራዎች ላይ እናተኩራለን።"

ጄሲካ ህክምናው በመዘግየቱ ሁኔታውን ይበልጥ አሳሳቢ አድርጎታል ብላ ታምናለች። "ሉካስ በርካታ ኢንፌክሽኖች ነበሩት። የሳንባው 70 በመቶ ተጎድቷል። ልቡ በ 40 በመቶ አድጓል። ይህ ሊወገድ የሚችል ነበር።"
ሉካስን ያከሙት ዶ/ር ሞንቴም በዚህ ይስማማሉ። ኤም አይ ኤስ መከላከል ባይቻልም ሁኔታው ከታወቀ እና ቀድሞ ከታከመ ህክምናው የበለጠ ስኬታማ ነው ይላሉ።
"ቀድሞ ህክምና ቢያገኝ ኖሮ የተሻለ ነው። በከባድ ህመም ነው ወደ ሆስፒታል የደረሰው። ቀደም ብለን ማከም ብንችል ኖሮ የተለየ ውጤት ሊኖረው ይችል ነበር ብዬ አምናለሁ።"
ጄሲካ ወሳኝ የሆኑ ምልክቶች ያላቸው ሰዎችን ለመርዳት የሉካስን ታሪክ ማካፈል ትፈልጋለች።
እንደ ዶ/ር ፋቲማ ማሪንሆ ከሆነ ልጆች ለኮቪድ ያላቸው የአደጋ ተጋላጭነት ዜሮ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ አለ። እጅግ በጣም በሚያስደንቅ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሕፃናት በቫይረሱ ተጠቅተዋል።
እንደ ብራዚል ጤና ሚኒስቴር ከሆነ ከጎርጎሮሳዊያኑ ከየካቲት 2020 እስከ 15 ሚያዝያ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ በኮቪድ-19 ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ 518 ሕፃናትን ጨምሮ እስከ ዘጠኝ ዓመት ዕድሜ ድረስ ያሉ 852 የሚሆኑትን የብራዚል ሕፃናት ሞተዋል።
ዶ/ር ማሪንሆ ግን ከዚህ ቁጥር ከሁለት እጥፍ በላይ የሚሆኑት በኮቪድ እንደሞቱ ይገምታሉ። ከኮቪድ ምርመራ እጥረት ጋር ተያይዞ ቁጥሮቹ ዝቅ ብለዋል ይላሉ።
ዶ/ር ማሪንሆ በወረርሽኙ ወቅት ባልተገለጸ አጣዳፊ የትንፋሽ ህመም ምክንያት የሟቾችን ብዛት በማስላት ከቀደሙት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር በ10 እጥፍ እንደሚጨምር ይገልጻሉ።
እነዚህን ቁጥሮች በመጨመር ቫይረሱ 1,302 ሕፃናትን ጨምሮ ከዘጠኝ ዓመት በታች የሆኑ 2,060 ሕፃናትን እንደገደለ ይገምታሉ።
ይህ ለምን ሆነ?
ባለሙያዎቹ እንደሚናገሩት በአገሪቱ በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው የብራዚል ሕፃናትን የመያዝ ዕድል ይጨምረዋል።
"ህጻናትን ጨምሮ ብዙዎች ሆስፒታል ገብተዋል ሕይወታቸውም አልፏል። ቫይረሱን መቆጣጠር ከተቻለ ይህ ሁኔታ ሊቀየር ይችላል" ሲሉ የብራዚል የሕፃናት ሕክምና ማኅበር የክትባቶች የሳይንስ ክፍል ፕሬዝዳንት ሬናቶ ክፉሪ ይገልጻሉ።
እንዲህ ዓይነቱ ከፍተኛ የመያዝ መጠን የብራዚልን አጠቃላይ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት አጥለቅልቆታል። በመላ አገሪቱ የኦክስጂን አቅርቦቶች ሲቀንስ የመሰረታዊ መድኃኒቶች እጥረትና በርካታ የጽኑ ህሙማን ክፍሎች ውስጥ አልጋ የለም።
የብራዚል ፕሬዝዳንት ጃየር ቦልሶናሮ የእንቅስቃሴ እገዳዎችን መቃወማቸውን የቀጠሉ ሲሆን ባለፈው ዓመት በሰሜን ብራዚል ማኑስ ውስጥ ፒ1 የተባለ የቫይረስ ዓይነት በጣም ተስፋፍቷል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከወረርሽኝ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር ባለፈው ወር የሞቱት ሰዎች ቁጥር በሁለት እጥፍ ያደገ ሲሆን ይህም እንደቀጠለ ነው።
ማሪንሆ እንደሚሉት ብዙውን ጊዜ የኮቪድ ምርመራው ለልጆች የሚደረገው በጣም በጠና በሚታመሙበት ጊዜ ዘግይቶ ነው።
"በሽታውን የመለየት ከባድ ችግር አለብን። ለሕዝቡ በቂ ምርመራዎች አናደርግም። የልጆችም ቢሆን አናሳ ነው። የምርመራው መዘግየት ስላለ ለህጻናቱ የሚደረገው እንክብካቤ ላይ መጓተት አለ።"
"ልጆች የበለጠ ተቅማጥ፣ በጣም ብዙ የሆድ ህመም እና የደረት ህመም አለባቸው። የምርመራው መዘግየት ስላለ ህጻናቱ ሆስፒታል ሲመጡ በከባድ ሁኔታቸው ተወሳስቦ ሞት ሊከሰት ይችላል" ይላሉ።
ድህነት እና የጤና እንክብካቤ ተደራሽ አለመሆንም ሌላው ምክንያት ነው።
የበሽታው ወረርሽኝ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ያሉ ልጆችን መጎብኘት ተከልክሏል።
በአልበርት ሳቢን የህፃናት ሆስፒታል ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ሲናራ ካርኔሮ እንዳሉት ይህ እጅግ ፈታኝ ነው። ወላጆች የልጆቻቸውን ስሜት ሊረዱ ስለሚችሉ ነው።
እንደ ዶ/ር ካርኔሮ ከሆነ "አንድ ልጅ ወላጆቹን ሳያይ ሲሞት ማየት ያማል" ብለዋል።
የአልበርት ሳቢን ሆስፒታል ሠራተኞች በወላጆች እና በልጆቻቸው መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻልና የቪዲዮ ጥሪዎችን ለማመቻቸት ስልኮችን እና ታብሌቶችን ለመግዛት ተሰባስበዋል።
እንደ ዶ/ር ካርኔሮ ከሆነ ይህ እጅግ አግዟቸዋል። "በቤተሰብ አባላት እና በታካሚዎች መካከል ከ100 በላይ የቪዲዮ ጥሪዎችን አድርገናል። ይህ ግንኙነት ጭንቀቱን በእጅጉ ቀንሶታል።"
የሳይንስ ሊቃውንት በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሞት አደጋ አሁንም "በጣም ዝቅተኛ" እንደሆነ ይገልጻሉ። አሁን ያሉት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከብራዚል 345,287 ሟቾች መካከል 0.58 በመቶ የሚሆኑት ከ 0-9 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው።
መቼ እርዳታ መጠየቅ ያስፈልጋል?
ኮሮናቫይረስ በልጆች ላይ ተላላፊ ቢሆንም ከባድ ግን አይደለም። ልጅዎ ጤናማ ካልሆነ ከኮሮቫይረስ ይልቅ በሌላ በሽታ ሊሆን ይችላል።
ሮያል የሕፃናት ሕክምና ኮሌጅ ወላጆች ልጆቻቸው ከዚህ በታች ያሉትን ምልክቶች ካሳዩ አስቸኳይ እርዳታ እንዲሹ ይመክራሉ።
- የቆዳ ቀለም መቀየር እና ቆዳ ሲነካ ያልተለመደ ቀዝቃዛ ስሜት ሲፈጠር
- አተነፋፈሳቸው ለአፍታ መቆም፣ መደበኛ ያልሆነ አተነፋፈስ
- በአተነፋፈስ፣ በመረበሽ ወይም ምላሽ ባለመስጠት ከባድ ችግር ካለ
- የከንፈሮች ዙሪያ ቀለም እየተቀየረ መሄድ
- በጣም መረበሸ፣ ያለማቋረጥ ማልቀስ፣ ግራ መጋባት፣ ለመነቃቃት መቸገር ወይም ምላሽ የማይሰጡ ሲሆን
- በተለይም በአሥራዎቹ ዕድሜ ባሉ ወንዶች የዘር ፍሬ ላይ ህመም ካለ
















