ኮቪድ-19፡ በአሜሪካ የሃብታሞቹ ትምህርት ቤት የተከተቡ ሠራተኞቹ እንዳይገቡ ከለከለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአሜሪካ ማያሚ ከተማ የሚገኝ ትምህርት ቤት የተከተበ ሠራተኛ ከተማሪዎች ጋር መገናኘት የተከለከለ ነው በማለት መምህራን የኮቪድ ክትባት እንዳይወስዱ እያበረታታ ነው።
የሴንተነር አካዳሚ ኃላፊዎች ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ያልተከተቡ ሰዎች ክትባቱን ከተከተቡት ጋር ሲገናኙ "አሉታዊ ተጽዕኖ" ያድርባቸዋል በሚል ነው።
ሆኖም ጽንሰ-ሐሳቡ በማስረጃ አለመደገፉን ባለሙያዎች ይናገራሉ። የአሜሪካ የጤና ባለሥልጣናት በበኩላቸው ክትባቶቹ አስተማማኝና ውጤታማ እንደሆኑ ተናግረዋል።
እስካሁን 141 ሚሊዮን የሚሆኑ አሜሪካውያን የኮቪድ -19 ክትባት ተከትበዋል።
በክፍያ ትምህርት የሚሰጠው ሴንተነር አካዳሚ በማያሚ ዲዛይን ወረዳ የሚገኝ ነው። ትምህርት ቤቱ ለመዋዕለ ህጻናት ተማሪዎች በዓመት 15,160 ዶላር ሲያስከፍል ከ13 እስከ 15 ዓመት ዕድሜ ላላቸው የመካከለኛ ደረጃ ተማሪዎች ደግሞ እስከ 30,000 ዶላር ክፍያ ይጠይቃል።
ከመስራቾቹ አንዷ የሆኑት ላይላ ሴንተነር በዚህ ወቅት የትምህርት ቤቱ ፖሊሲ የኮቪድ -19 ክትባት የወሰደ ሰው አለመቅጠር ነው ሲሉ ለወላጆች መግለጻቸውን ሲቢኤስ ማያሚ ዘግቧል።
ጉዳዩን ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበው ኒው ዮርክ ታይምስ ነበር። በዘገባው መሠረት አካዳሚው ሴንትነር ለሠራተኞቹ በጻፈው ደብዳቤ መምህራን ክትባቱን ስለመውሰዳቸው ለትምህርት ቤቱ ማሳወቅ እንዳለባቸው ገልጿል።
"ተጨማሪ መረጃ እስከሚገኝ ድረስ በቅርቡ የተከተቡ ሠራተኞች ተማሪዎቻችን አጠገብ ዝር እንዲሉ መፍቀድ አንችልም" ብለዋል።
በመሆኑም ከትምህርት ዓመቱ ማብቂያ በኋላ ክትባቱን ለመውሰድ የሚጠብቁ መምህራን ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ የሚፈቀድላቸው በክትባቱ ላይ ክሊኒካዊ ሙከራዎች ሲጠናቀቁ ብቻ ነው።
በተጨማሪም ሴንትነር ክትባቱን የተከተቡ ሰዎች ባልተከተቡ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ አድርሰዋል የሚል ሃሰተኛ ማስረጃ በመደጋገም አቅርበዋል። ለዚህም ማስረጃቸው ሦስት የትምህርት ቤቱ ሴት ሠራተኞች "ከተከተቡ ሰዎች ጋር ካሳለፉ በኋላ የወር አበባ ዑደታቸው ተዛብቷል" የሚል ነው።
በጉዳዩ ላይ ምንም ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም። በአሜሪካ የጸደቁት የኮሮናቫይረስ ክትባቶች ከመካንነት፣ ፅንስ ማስወረድ ወይም በሴቶች የስነ ተዋልዶ ጤና ማንኛውንም አሉታዊ ለውጦች ጋር ግንኙነት የላቸውም።
ወይዘሮ ሴንትነር እና ባለቤታቸው ዴቪድ ሴንትነር ራሳቸውን "የጤና ነፃነት ተሟጋቾች" እንደሆኑ ይገልጻሉ።
ወ/ሮ ሴንትነር በፌስቡክ ገጻቸው ላይ የፀረ-ክትባት ይዘት ያለውን መረጃ በተደጋጋሚ እንደሚያካፍሉ ታይምስ ዘግቧል።
የወ/ሮ ሴንትነር ተወካይ ከአሜሪካ ሚዲያ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ትምህርት ቤቱ "የኮቪድ ክትባቶች ደህንነታቸው የተጠበቀ ስለመሆኑ መቶ በመቶ እርግጠኛ አለመሆኑን እና በዚህ ወቅት ምቾት እንዲሰማን የማያደርጉ ብዙ የማይታወቁ ተለዋዋጭ ነገሮች አሉ" ብለዋል።
በአካባቢው የሚገኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ የመምህራን ኅብረት ለሲቢኤስ ዜና በሰጠው መግለጫ "እንደዚህ ባሉ ትምህርት ቤቶች ያሉ የሥራ ባልደረቦቻችን በሠራተኛ ማኅበር አለመወከል እና በውል መብቶች እጥረት ሊቋቋሙት በማይችሉት የደህንነት እና የሠራተኛ መብት ጥሰቶች በጣም ተሰምቶናል" ብሏል።












