ኮሮናቫይረስ፡ የአሜሪካውያን የኮቪድ-19 ክትባት ምርጫ ለምን የተለያየ ሆነ?

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ ሦስት ክትባቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የፈቀደች ሲሆን ሰዎች የሚፈልጉትን እየመረጡ ነው።

ሦስቱም የኮቪድ-19 ክትባቶች በቫይረሱ መያዝና ተይዞ ሆስፒታል መግባትን እንዲሁም ሞትን በመከላከል ረገድ ውጤታማ መሆናቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ የጤና ባለሥልጣናት ለዜጎች የሚሰጠው የተሻለው ክትባት ነው ብለዋል።

ቢሆንም ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ይልቅ ፋይዘር እና ሞደርና ክትባቶችን የሚመርጡ ብዙዎች ናቸው።

በመጋቢት መጀመሪያ የዲትሮይት ከንቲባ ማይክ ዱጋን የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባትን ውድቅ አድርገው በአሜሪካ የቀረቡት ሌሎች ሁለት ክትባቶች የተሻሉ መሆናቸውን ለከተማዋ ነዋሪዎች ጠቁመዋል።

በጋዜጣዊ መግለጫቸው ወቅት "የዲትሮይት ከተማ ነዋሪዎች የተሻለውን እንዲያገኙ የተቻለኝን ሁሉ አደርጋለሁ" ብለዋል።

የጤና ባለሙያዎች አስተያየት ከሰጡ በኋላ ከንቲባው ክትባቱ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ ስለመሆኑ "ሙሉ እምነት አለኝ" በማለት ገልጸዋል።

እንደ ዱጋን ሁሉ አንዳንድ አሜሪካውያን ስለ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት እና ስለ አጠቃላይ ውጤታማነቱ ጥያቄ አንስተዋል። የጤና ባለሥልጣናት ግን እነዚህ ቁጥሮች ሙሉውን ገጽታ እንደማያሳዩ አስጠንቅቀዋል።

አንዳንዶች ጆንሰን ኤንድ ጆንሰንን ከመውሰድ ሳይከተቡ ቢዘገዩ እንደሚመርጡ ይናገራሉ።

አንድ የዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ ለቢቢሲ ሲናገሩ "የክትባት ቀጠሮ በነበረኝ ጊዜ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰንን እየሰጡ እንደሆነ ስለሰማሁ ሰርዤዋለሁ። ያንን ክትባት በጭራሽ አልወስድም" ብለዋል።

እንደ ዶ/ር ማይክል አንድራሲክ ያሉ የጤና ባለሥልጣናት ማንኛውንም ፈቃድ ያገኘ ክትባት መውሰድ ጥሩ መሆኑን አሜሪካውያንን ለማሳመን እየሞከሩ ነው።

"በአንድ በኩል ሰዎች ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጥ በመሆኑ በጣም ተደስተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ውጤታማነቱን በተመለከተ ብዙ ግራ መጋባት አለ። ይህ ደግሞ ጥሩ አይደለም" ሲሉ በፍሬድ ሃች የክትባትና ተላላፊ በሽታ ክፍል ከፍተኛ የሳይንስ ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር አንድራሲክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአሜሪካ ተቆጣጣሪዎች አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰጠውን ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት በይፋ ያጸደቁት በየካቲት ነው። ይህም ፍቃድ ያገኘ የመጨረሻው ክትባት አድርጎታል።

አዲስ የኤም አር ኤን ኤ ክትባት ቴክኖሎጂን ከሚጠቀሙት እና ሁለት ጊዜ ከሚሰጡት ከፋይዘር እና ከሞዴርና ክትባቶች በተለየ መልኩ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ጉዳት እንዳያደርስ የተደረገ ቫይረስን ይጠቀማል።

ከዚያ የኮሮናቫይረስን ዘረ መል በከፊል ወደ ሰውነት ይወስዳል። ይህም ሰውነት አደጋውን ለይቶ እንዲያውቅ እና ኮሮናቫይረስን ለመዋጋት እንዲዘጋጅ ያደርጋል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በክትባቱ ላይ እምነት እንዳላቸው አሳይተዋል፡፡ በዚህ ወር ለአሜሪካኖች ከቀረበው በእጥፍ 100 ሚሊዮን ተጨማሪ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቶች እንደምታዝ አስታውቀዋል።

የብሔራዊ አለርጂ እና ተላላፊ በሽታዎች ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ በበኩላቸው በአሜሪካ የሚገኙ ሁሉም ክትባቶች ጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባትም "ደካማ ክትባት አይደለም" ብለዋል።

አሳሳቢው ነገር ከሙከራዎች የሚወጣው የውጤታማነት መረጃ መለያየት ነው።

የጤና ባለሥልጣናት ሦስቱም ክትባቶች መቶ በመቶ ቫይረሱን የመከላከል አቅም አላቸው ሲሉ አሳስበዋል።

የፋይዘር እና የሞደርና ክትባቶች አዳዲሶቹ የቫይረሱ ዝርያዎች ከመስፋፋታቸው በፊት የተሞከሩ ሲሆን አዳዲሶቹ ዝርያዎች በሙከራዎች ላይ ልዩነት ይፈጥራሉ።

በተጨማሪም የአሜሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል (ሲዲሲ) ሁሉም ክትባቶች ከዓመታዊው የጉንፋን ክትባት የበለጠ ውጤታማ ናቸው ሲል ይገልጻል።

እንደ ዶ/ር አንድራስክ ከሆነ "ዋናው ነገር ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን፣ ሞደርና እና ፋይዘር ከባድ በሽታን በመከላከል፣ ሆስፒታል መተኛትን በመቀነስ፣ ከፍተኛ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን በመቀነስ ወይም መሞትን በመከላከል በማይታመን ሁኔታ ውጤታማ ናቸው።"

የማኅበረሰብ ጤና ተሟጋቾች እንደሚሉት ከሆነ ሌላው የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ጠቃሚ ጎን በአሜሪካ ውስጥ ብቸኛው አንድ ጊዜ የሚሰጥ ክትባት መሆኑን ነው።

ራቅ ወዳሉ እና ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑ ቦታዎችም ለማሰራጨት የበለጠ ምቹ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ያንን ክትባት ብቻ ወደ አካባቢዎቹ መላክ መገለልን ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለ።

አክለውም "ሁሉም ክትባቶች ለሁሉም ሊደርሱ ይገባል ብዬ አስባለሁ። ጆንሰን ኤንድ ጆንሰንን ወደ ገጠር እና ድሃ ማኅበረሰቦች የመላክ ምክንያታዊነት በእንክብካቤ ተደራሽነት ምክንያት ነው ብዬ አስባለሁ" ብለዋል ዶ/ር አንድራስክ።

እንደ ዶ/ር አንድራስክ ያሉ የማኅበረሰብ አመራሮች እና የጤና ባለሙያዎች በክትባቱ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋፋት እና የተሳሳተ መረጃን ለመከላከል ጥረት እያደረጉ ነው።

በአሜሪካ ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ሲሞቱ "የእኔ ተራ ሲደርስ ማንኛውንም ክትባት እወስዳለሁ" ይላሉ።

ሌሎቹ አሳሳቢ ጉዳዮችስ ምንድን ናቸው?

ዩ ኤስ ኮንፈረንስ ኦፍ ካቶሊክ ቢሾፕስ የተባለው እና በአሜሪካ የሚገኘውን ቤተክርስትያን የሚወክለው ጉባኤ በክትባቱ ዙሪያ "የሞራል ስጋት" መኖሩን መግለጹ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የስጋቱ ምንጭ ጽንስ በማስወረድ ከሚገኙ ሕዋሶች ክትባቱ ተመርቷል መባሉ ነው።

ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኢቦላ ክትባትን ለማዘጋጀት የዋለውን ተመሳሳይ ዘዴ ተጠቅሟል። በተጨማሪም የትኛውም የኮቪድ -19 ክትባት ምንም ዓይነት የሰው ህዋሳትን አልያዘም።

ጉባኤው ምርጫ እስካለ ድረስ ካቶሊኮች አማራጭ ክትባቶች መውሰድ እንዳለባቸው መክሯል።

በአሜሪካ ጉባኤ የተሰጠው ምክር ከቫቲካን አቋም ጋር የሚቃረን ይመስላል። ምክንያቱም ቫቲካን እንዲህ ያሉት ክትባቶች "ከሞራል አንጻር ተቀባይነት አላቸው" ስለምትል ነው።

ሌሎች የካቶሊክ መሪዎችም የቤተክርስቲያኗ አባላት ከዚህ ክትባት መራቅ አለባቸው የሚለውን ሐሳብ እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል።

የሐርትፎርድ ሊቀ ጳጳስ እና ሌሎች የአካባቢው የሐይማኖት አባቶች በሰጡት መግለጫ ሁሉም ነዋሪዎች ለራሳቸው ጤና እና ለጋራ ጥቅም ሲሉ "ማንኛውንም ክትባት ለመቀበል የህሊና ነፃነት ሊሰማቸው ይገባል" ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ዶሮ በሽታ እና ሩቤላ ያሉ ሌሎች ብዙ ክትባቶች በተመሳሳይ መልኩ የተሠሩ ቢሆንም የካቶሊክ መሪዎች ስለ ለጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ያሰሙት ስጋት በአንዳንድ አሜሪካውያን ዘንድ ጥርጣሬ እንዲጨምር አድርጓል።

ስጋቶችን የሚጋፈጠው የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት ብቻ አይደለም። አሜሪካ ጥቅም ላይ እንዲውል ለመፍቀድ እየተዘጋጀችበት የሚገኘው የኦክስፎርድ-አስትራዛኔካ ክትባት ከደም መርጋት ችግር ጋር በተያያዘ የአውሮፓ አገራት ታግዶ ነበር።

የአውሮፓ ሕብረት የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ባሥልጣን ክትባቱ "ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ ነው" ብሎ መግለጹን ተከትሎ ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን እና ስፔን ክትባቱን መጠቀም መጀመራቸውን ተናግረዋል።