የኮሮናቫይረስ ክትባትና ሐሰተኛ ሰነድ በድብቅ እየተሸጠ ነው

የክትባት ብልቃጥና ስሪንጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኮሮናቫይረስ ክትባት፣ መከተብን የሚያሳዩ ሰነዶችና ሐሰተኛ ከኮቪድ-19 ነጻ የምስክር ወረቀቶች በስውሩ የበይነ መረብ መድረክ [ዳርክኔት] ላይ እየተቸበቸቡ ነው።

በአሁኑ ጊዜ እየተሰጡ ያሉት የተለያዩ የክትባት አይነቶች ዋጋ ወጥቶላቸው ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን፤ የአስትራዜኒካ፣ ስፑትኒክ፣ ሲኖፋርም ወይም ጆንሰን ኤንድ ጆንስን ክትባቶች ከ500 አስከ 750 ዶላር እየተሸጡ መሆኑ ተነግሯል።

በተጨማሪም በዚህ ድብቅ የኢንተርኔት የግብይት መድረክ ላይ ለጉዞና ለሌሎች ምክንያቶች የሚፈለገው የኮሮናቫይረስ ክትባት መውሰድን የሚያመለክተውን ሰነድ አስከ 150 ዶላር በሆነ ወጪ መግዛት ይቻላል።

ቢቢሲ ለሽያጭ የቀረቡት ክትባቶች ትክክለኛ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ባይችልም፤ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ግን በዚህ ስውር የግብይት መድረክ ላይ ከክትባት ጋር የተያያዙ ማስታወቂያዎች በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

ይህ ዳርክኔት ወይም ዳርክ ዌብ የሚባለው ድብቅ የኢንተርኔት የግብይት መድረክ በተወሰኑ የበይነ መረብ ማሰሻ መጠቀሚያዎች በኩል ብቻ ሊደረስበት የሚችል ነው።

የበይነ መረብ ደኅንንት ምርምር ተቋሙ 'ቼክ ፖይንት' ካለፈው ጥር ጀምሮ የክትባት ሽያጭ ማስታወቂያዎች መታየት እንደጀመሩ አመልክቷል።

የክትባት ሽያጩን በተመለከተ በተከታታይ ጭማሪ አሳይቶ በሦስት እጥፍ በማደግ ከ1,200 በላይ ማስታወቂያዎች ቀርበዋል።

ይህንን የክትባት ሽያጭ የሚያካሂዱት ከአሜሪካ፣ ከስፔን፣ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይና ከሩሲያ ሲሆኑ፤ በርካቶቹ ማስታወቂያዎች በሩሲያ ቋንቋና በእንግሊዝኛ የቀረቡ ናቸው።

በክትባቶቹ ማስታወቂያዎቹ ላይ ለተለያዩ ክትባቶች የተለያየ ዋጋ የወጣላቸው ሲሆን፤ በኢትዮጵያ እየተሰጠ ያለው የኦክስፎርድ-አስትራዜኒካ ክትባት 500 ዶላር፣ የጆንሰን ኤንድ ጆንሰን እና ስፑትኒክ ክትባት እያንዳንዳቸው በ600 ዶላር እንዲሁም ሲኖፋርም ደግሞ 750 ዶላር ይሸጣሉ ተብሏል።

አንድ የክትባት አቅራቢ ማስታወቂያ እንደሚለው ክትባቱን የሚፈልግ ሰው ትዕዛዝ በሰጠ በቀጣዩ ቀን በአስቸኳይ እንሚያቀርብ ገልጿል።

ሐሰተኛ የኮቪድ-19 የምርመራ ውጤት የሚሰጥ አንድ አስተዋዋቂ ደግሞ ለገዢዎች እንዲህ ሲል ማበረታቻ እንደሚሰጥ ገልጿል።

"ለተጓዦች፣ ለአዲስ ሥራ ተቀጣሪዎችና ለሌሎችም ከኮሮናቫይረስ ነጻ ስለመሆናቸው የምርመራ የምስክር ወረቀት እንሰጣለን። ሁለት የምስክር ወረቀቶችን ለሚገዙ ሦስተኛውን በነጻ እናዘጋጃለን" ይላል።

ከምርመራ ውጤት ጎን ለጎን የክትባት የምስክር ወረቀት አስፈላጊ እየሆነ ነው። በተለይ የክትባት ምስክር ወረቀት ወደ ቡና ቤቶች ወይም የስፖርት ስታዲየሞች ለመግባት ይጠየቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሐሰተኛ የክትባት ማረጋገጫ ሰነድና የምርመራ ምስክር ወረቀት በበይነ መረብ ስውር የግብይት መድረክ ላይ የሚሸጥ ሲሆን፤ ክፍያውም ለይቶ ለማወቅ አስቸጋሪ በሆነ መንገድ የኢንተርኔት የክፍያ መንገድ ቢትኮይን አማካይነት የሚፈጸም መሆኑን በሽያጩ ላይ ምርመራ ያደረጉት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ይህንን ሽያጭ ከሚከታተሉት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት ኦዲድ ቫኑኑ ሲናገሩ "የክትባትም ሆነ የምርመራ ሐሰተኛ ሰነዶችን እንዲሁም ክትባትን በዚህ መንገድ ለመግዛትመሞከር አደገኛ ነው" በማለት ምክንያቱን ሲያስረዱ "የበይነ መረብ መረጃ መዝባሪዎች በዚህ መንገድ የሰዎችን ግላዊ መረጃዎችን በመውሰድ ለዝርፊያ ሊዳርጉ ይችላሉ" ብለዋል።

ባለሙያው ከቡድናቸው ጋር በሽያጩ ላይ ምርመራ ሲያደርጉ 750 ዶላር ከፍለው የሲኖፋርም ምርት የሆነውን ክትባት ያዘዙ ቢሆንም እስካሁን ክትባቱ እንዳልደረሳቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጥናት ቡድኑ እንደሚለው ክትባቶቹን እናቀርባለን በማለት ማስታወቂያ የሚያስነግሩት የሚሸጡት ክትባት ትክክለኛ ይሁን አይሁን እርግጠኛ መሆን አይቻልም።

ጨምረውም አገራት ከክትባትና ከምርመራ ጋር በተያያዘ ለማረጋገጫነት የሚሰጧቸው ሰነዶች ተመሳስለው እንዳይዘጋጁ የሚያስችል ዘዴን እንዲቀይሱ አሳስበዋል።