ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካውያን ወደ 80 በመቶ የአለማችን አገራት እንዳይጓዙ ተመከሩ

ኒውዚላንድ ኦክላንድ አየር መንገድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ አሜሪካውያን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ 80 በመቶ የአለማችን አገራት እንዳይጓዙ መክሯል።

የጉዞ ምክሮችን አስመልክቶ ቢሮው ለሚዲያዎች በላከው መግለጫ ወረርሽኙ "ለተጓዦች ከፍተኛ አደጋ ደቅኖባቸዋል" ብሏል፥።

እስካሁን ድረስ አሜሪካ ዜጎቿን እንዳትጓዙ ብላ አውጥታቸው የነበሩ አገራት ዝርዝር 34 ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙ ያለው ስጋት ከፍተኛ በመሆኑ ዝርዝሯን ማሻሻሏን አሳውቃለች።

የኮቪድ-19 ከተነሳባት እለት ጀምሮ ሶስት ሚሊዮን ሰዎች በአለማችን ሲሞቱ ከነዚህም ውስጥ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት አሜሪካውያን ናቸው።

የአለም ጤና ድርጅት ከሰሞኑ አለማችን "የወረርሽኙ ሁኔታ ደርሶ የማያውቅበት ጣራ ላይ በቅርቡ" እንደሚደርስ አስጠንቅቋል። ምንም እንኳን የክትባት ፕሮግራሞች መሳ ለመሳ ቢሄዱም ወረርሽኙ ማሻቀቡ አይቀርም ብሏል ድርጅቱ።

ባገረሸው ሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ እየተናጠች ያለችው ህንድ ወረርሽኙን ከዚህ በላይ ከማሻቀብ ለመግታት በሚል እድሜያቸው ከ18 በላይ የሆኑ ዜጎቿን ሁሉ እንደምትከትብ አስታውቃለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ክፍል ይህ የጉዞ ዝርዝሩን ማሻሻል ያስፈለገበት ምክንያት ከበሽታዎች ቁጥጥርና መካላከል ማዕከል (ሲዲሲ) ጋር ለማጣጣም እንደሆነ አስታውቋል።

ይህም ማለት ግን ዜጎቿ እንዳይጓዙ የተመከሩባቸው አገራት "የጤና ሁኔታ እንደገና ተገምግሞ እንዳልሆነም" ተገልጿል።

ነገር ግን በአሁኑ ወቅት አሜሪካ 80 በመቶ አገራት ዜጎቿ እንዳይጓዙ ብላ ያስጠነቀቻቸው አገራት በወረርሽኙ ምደባ መሰረት ደረጃ አራት የተቀመጡ ናቸው ተብሏል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ግምገማ መሰረት በዝቅተኛ ደረጃ የተቀመጡ አደራት ማካው፣ ታይዋንና ኒውዚላንድ ሲሆን እነዚህ አገራት ሙሉ በሙሉ ወረርሽኙን ተቆጣጥረዋል የተባሉ አገራት ናቸው።

አንታርክቲካም ብትሆን ደረጃ ሁለት ላይ የተቀመጠች ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ ደረጃ ሶስት ላይ ናት።

ደረጃ ሁለት የተቀመጡ አገራት ከጥንቃቄ ጋር አሜሪካውያን እንዲጓዙ የተመከሩ ሲሆን ደረጃ ሶስት ላይ ደግሞ መጓዝ ከሌለባቸው ደግሞ ተሰብስበው ቢቀመጡ ብሏል።

ሲዲሲ በአጠቃላይ አሜሪካውያን ከክትባት በኋላ የአገር ውስጥ ጉዞዎችን ቢያደርጉ አለም አቀፍ ጉዞዎች ደግሞ ቢከተቡም "ለአደጋ ይጋለጣሉ" ብሏል።